"ኢትዮጵያ ከምርጫው፤ የሚከበር የምርጫ ቦርድ እና ለዴሞክራሲ ዘብ የሚቆም መራጭ አትርፋለች" ... ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

122

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚከበር የምርጫ ቦርድ፣ ለዴሞክራሲ ዘብ የሚቆም ጠንካራ መራጭ፣ ግፊትና ጫናን መቋቋም የሚችሉ ብርቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አትርፋለች ሲል ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገረ።

"ኢትዮጵያዊነት በርቱዓዊነት" በአዲስ አበባ ለመረጠው ሕዝብ የምስጋና መድረክ አካሂዷል።

ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት "ኢትዮጵያዊነት በርቱዓዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ በ"ሐ" የምርጫ ምልክት በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 28 ተወዳድሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሸነፉ ይታወቃል።

በዛሬው የምስጋና መድረክም ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እርሱንና ሃሳቡን ደግፎ ለመረጠው ሕዝብ ምስጋና አቅርቧል።

ዲያቆን ዳንኤል ባደረገው ንግግር በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በታላቁ አሸንፋለች ብሏል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል በቀጣይ ሕገ መንግስቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕጎች እንዲፈተሹና በሰፋ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሻሻሉ ፍላጎትና ምኞቱ መሆኑን ገልጿል።

አሸናፊው ፓርቲና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመካከሩበት፣ ለኢትዮጵያ እድገት፣ ልማትና አንድነት በጋራ የሚሰሩበት እድል እንዲፈጠር የበኩሉን እንደሚያበረክትም ነው የተናገረው።  

በመድረኩ ተገኝተው ሐሳባቸውን ያጋሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሑር ዶክተር ዳኛቸው አሠፋ፤ ኢትዮጵያ ትክክለኛ፣ ፍትሃዊና ታማኝ ምርጫ ማካሄዷን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ለኢትዮጵያ መልካም የማይመኙ አንዳንድ የውጭ አገራት ምርጫውን በአዎንታዊ መንገድ አለቀበላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ግን ይህን ክፉ ሐሳብ ባለመቀበል ምርጫው አገሪቷ አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደችበት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መጋቢ ሃዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት "ሕዝብ በሞራል እንዲታነጽ አበርክቶ ያለው፤ በእኩልነት የሚያምንና ለዚህም ሲሰራ የኖረ ነው" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያዊነት በርቱዓዊነት" ኢትዮጵያዊነትን ከጭቆና፣ ከተዛባ ትርክት፣ ከእርስ በእርስ ግጭት፣ ከአጉል ፉክክርና ከኢ-ፍትሃዊ ጥቅመኝነት ይልቅ በወንድማማችነትና በትብብር መነጽር ማየትና ማጽናትን ዓላማ ማድረጉ በመድረኩ ተነግሯል።

በምስጋና መርሃ-ግብሩ ምሑራን፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የመዲናዋ ነዋሪዎች ታድመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም