ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል ... ዶክተር ካሊድ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል ... ዶክተር ካሊድ አህመድ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ሥነ-ምህዳርና ሬጉላቶር ክፍል ሃላፊ ዶክተር ካሊድ አህመድ ገለጹ።
የሃሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ህልውና ከመጉዳት ባሻገር የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ እንደሚጥል ይታወቃል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ሃሰተኛ መረጃ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እየተሰራጨ ይገኛል።
"ይህን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?" ስንል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ሥነ-ምህዳርና ሬጉላቶር ክፍል ሃላፊ ዶክተር ካሊድ አህመድን ጠይቀናል።
ሃላፊው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ከሚተላለፉት መረጃዎች መካከል ገንቢና እውቀት የሚገኝባቸው የመኖራቸውን ያክል ጥፋትና ድብቅ ዓላማ ያነገቡም አሉ።
በአሁኑ ወቅት የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ አድርገው "ትክክለኛ ያልሆኑ፣ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች በብዛት ይሰራጫሉ፤ እየዘመነ መጣውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የማደናገር ስልታቸው እያደገ መጥቷል" ብለዋል።
ነገሮችን በጥልቀት የሚያይና ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ህብረተሰብን የመፍጠር ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ሊያስተውሉት የሚገባው ነጥብ ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን ሃሳብ የሚያስተላለፍበት በመሆኑ ያገኙትን መረጃ ለሌሎች ከማጋራታቸው በፊት “ከየት ነው? እንዴት ነው?” የሚለውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ካሊድ አጽንኦት የሰጡት።
ማህበረሰብን ያሳተፈ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም "የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራት አለበት" ነው ያሉት።
''በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ማቆም አይቻልም'' ያሉት ዶክተር ካሊድ፤ የተጠቃሚውን ግንዛቤ በማሳደግ መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል።