የአገር መከላከያ ሠራዊት በሚገኝበት ግንባር ሁሉ ተገኝተን ኃላፊነታችንን እንወጣለን – የጤና ባለሙያዎች

1451

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 17/2013 ( ኢዜአ)  የአገር መከላከያ ሠራዊት በሚገኝባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች ሁሉ በፈቃደኝነት በመሄድ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

ወታደርና የጤና ባለሙያ ተልዕኮው ጊዜና ቦታ የሚገድበው አይደለም ያሉት የጤና ባለሙያዎቹ ለአገሩና ለሕዝቡ ደጀን ለሆነው የመከላከያ ሠራዊት አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።

የጠቅላላ ሕክምና ዶክተር ሞላወርቅ አየለ የጤና ትምህርት ሲማር አገሩንና ሕዝቡን በቀናነት ለማገልገል ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን ይናገራል።

በተለይም የጤና ባለሙያነት ሙሉ ጊዜን በመስጠት የሚሰራና የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ነው የገለጸው።

በኮቪድ-19 መከሰት ወቅት በፈቃደኝነት በጽኑ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከላት ታካሚዎችን ለመርዳት ሳይሰለች መስራቱን ጠቅሷል።

ዶክተር ሞላወርቅ አሁንም በግንባር ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ያሉበት ድረስ በመሄድ የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ጥያቄ ማቅረቡንም ገልጿል።

ነርስ እዮብ ሃይለማርያም በበኩሉ በወጣትነቱ የተሻለ ሥራ ሰርቶ ደማቅ ታሪክ ለመጻፍና ለትውልድ ለማስተላለፍ በብርቱ እንደሚሰራ ተናግሯል።

ቀደም ሲል በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለተሰማሩ ሙያተኞች የሕክምና እርዳታ ለመስጠት በበጎ ፈቃደኝነት በመጓዝ ለወራት ማገልገሉን አስታውሷል።

በዚህም ለሕዳሴ ግድቡ ባለው አቅም ከማገዝ ባሻገር በሙያው ባበረከተው አስተዋጽኦ ኩራት እንደሚሰማው ነው የገለጸው።

አሁንም የአገር ህልውና በማስከበር ላይ ለሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግና አሻራውን ለማኖር ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

የሕክምና ትምህርት አንዱ ዓላማው ሕዝብን በሙሉ አቅም ማገልገል ነውና ድንበርና ወሰን ሳይለየው ለማገልገል መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ነርስ ታጋይ አሰጋ ነው።

የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ያለማወላወል የመከላከያ ሠራዊቱን የማገዝ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 ምላሽ ማዕከል የጤና ተቋማት ዝግጁነት አስተባባሪ አቶ ሔኖክ ኃይሉ እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት በነበረበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች ሳይታክቱ መስራታቸውን አውስተዋል።

በዚህ አስጨናቂ ወቅት በአገር ህልውና ላይ የተጋረጠውን ፈተና ለመመከት ግንባር ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በሕክምና ለመርዳት የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው በማቅናት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል እያበረከቱም ይገኛሉ ብለዋል።

አሁንም የጤና ባለሙያዎች ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚበረታታ በመሆኑ ተጨማሪ ጥሪዎችን በአዎንታ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።