ቀጥታ፡

አሜሪካ እጇን ከኢትዮጵያ ላይ ማንሳት አለባት…ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን

ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) አሜሪካ እጇን ከኢትዮጵያ ላይ ማንሳት አለባት በማለት የብላክ አጀንዳ ሪፖርት አዘጋጅ እና የምርመራ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን ገለጸች።

የብላክ አጀንዳ ሪፖርት አዘጋጅ እና የምርመራ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከአርቲ ቴሌቭዥን ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች።

ጋዜጠኛዋ በነበራት ቃለምልልስ አሜሪካ ላለፉት 27 ዓመታት ህወሓትን ስትደግፍ እንደቆየች ትገልጻለች።

አሁን በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራው የህወሓት ቡድን ከህዝብ በተነሳ ተቃውሞ ቀደም ሲል የነበረውን ስልጣን እንዲያጣ በመገደዱ አመራሮቹ ወደ ትግራይ ተሰባስበው እንደነበር ትጠቁማለች።

ወደ ትግራይ የተሰባሰበው የህወሓት ጁንታ አመራር ባለፈው ጥቅምት ወር በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን በዝርዝር ታስረዳለች።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ማናቸውም የምእራብ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሊሰጡት እንዳልፈለጉ የሚትገልጸው ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን፤ ይህን ዓይነት ጥቃት ሲፈጸም በዝምታ የሚያልፍ ሀገር የትም ቦታ ላይ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም ትላለች።

ይህንን እውነታ ወደ ጎን በመተው ምእራባውያን ሀገራት እና መገናኛ ብዙሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጦርነት እንዳስጀመሩ አድርገው እየዘገቡ እንደሚገኙ ገልጻ፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወደ አስመራ ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃት ፈጽሞ እንኳ ምእራባውያን በዝምታ ማለፋቸውን አመልክታለች።

በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተንኳሽነት ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ እንደተጎዳ በመግለጽ በመንግስት ላይ ያልተገባ ጫና እያሳደሩ ነው በማለት ገልጻለች።

ምእራባውያኑ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክተው የዘር ማጥፋት እንደተፈጸመ፣ ከፍተኛ ረሃብ እንደተከሰተ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትና ዘረፋ እየተፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ ጉዳዩን ከሚገባው በላይ በማጋነን እስካሁን ድረስ መንግስትን እየወነጀሉ መሆኑን ነው ጋዜጠኛዋ ያስረዳችው።

አሜሪካ በሌላ ሀገር እጇን ለማስገባት በምታስብበት ወቅት ሁልጊዜ የምትጠቀምበት ስልት አሁን በኢትዮጵያ ላይ የጀመረችው ዓይነት መሆኑንም ነው ጋዜጠኛዋ ያመለከተችው።

“አሜሪካ ከዚህ በፊት በሊቢያ እና በሶሪያ የወሰደችው እርምጃ ውጤቱን አሁን እያየነው ነው” በማለትም አክላለች።

አሜሪካ በሰብአዊ መብት ሽፋን በሌሎች ሀገራት ጣልቃ በመግባት ያልተገባ ተጽእኖ እንደሚትፈጥር ሩዋንዳን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አሜሪካ ያሳደረችው አሉታዊ ተጽእኖን ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን በዝርዝር አብራርታለች።

ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን “አሜሪካ እጇን ከአፍሪካ ላይ ማንሳት አለባት” በማለት በነበራት ቃለምልልስ በአጽንኦት አንስታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም