በበጀት ዓመቱ ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባድ ቁሳቁሶች ተይዘዋል

75

ሐምሌ 16/ 2013 (ኢዜአ) በ2013 በጀት ዓመት በተሠራው ጠንካራ የኮንትሮባድን ቁጥጥር ሥራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ላቀ አያሌው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ገለጹ፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከገቢና ከወጭ ኮንትሮባንድ ብር 2 ቢሊዮን 679 ሚሊዮን 116ሺ 304 ብር ለማዳን ታቅዶ 3 ቢሊዮን 635ሚሊዮን 992ሺ 9 ብር ከኮንትሮባንድ እንዲድን ተደርጓል፡፡

የእቅድ አፈጻጸሙም 135.72 በመቶ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም ውስጥ ግምታዊ ዋጋቸው ብር 3 ቢሊዮን 002ሚሊዮን 140ሺ 230 የሚገመቱት የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እዲሁም ግምታዊ ዋጋቸው ብር 633ሚሊየን 851ሺ 868 የሚገመቱት ደግሞ ወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች ናቸው።

ክንውኑ ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር በብር 1.2 ቢሊዮን እድገት ማሳየቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የኮንትሮባንድ ቁጥጥር አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

ለውጤቱ መመዝገብ የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችና ሠራተኞች በየበረሃው በቀንና በሌሊት እንዲሁም በፀሐይና በቁር ሳይሰለቹ መሥራት በመቻላቸው፣ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የጸጥታ መዋቅርና አመራር እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፓሊስ በሀገር ወዳድነት ስሜት በመስራታቸው፣

ህዝብ ጥቆማ በመስጠትና በመያዝ ሂደቱ በመተባበሩ የተሠራ ሥራ በመሆኑ ሁሉም መመስገን አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም ከዚህ በላይ የተሻለ ሥራ በመሥራት ኮንትሮባንድ የሀገር ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ሁሉም ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም