የአንበሳ ግቢ አንድ አንበሳ ብቻ ቀረው

1263

ሐምሌ 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው አንበሳ ግቢ ፓርክ ውስጥ አንድ አንበሳ ብቻ ቀርቷል።

አንበሳ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንደ ብሔራዊ ኩራት ተደርጎ የሚታይ እንስሳ ነው።

አንበሳን አርማቸው ያደረጉ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በርካታ ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያዊያን የመገበያያ ሳንቲሞችና የብር ኖቶች ላይም ይህ ባለ ግርማ ሞገስ እንስሳ ታትሞ ይገኛል።

ከአንበሳ ጋር በተገናኘ በ1941 ዓ.ም እንደተቋቋመ የሚነገርለት በአዲስ አበባ 6 ኪሎ አካባቢ የሚገኘው ‘አንበሳ ግቢ’ በውስጡ በርካታ አንበሳዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳትን ይዞ ቆይቷል።

የአንበሳ ግቢ እድሜ ጠገብ አንበሶችን ጨምሮ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ ኤሊ፣ ሳላ እና ሌሎች የዱር እንስሳትን የያዘ መካነ እንስሳ ነው።

ግቢው ከአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ነዋሪዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ከውጭ የሚመጡ ግለሰቦች ስፍራውን ይጎበኙታል።

በግቢ ከነበሩት አንበሶች መካከል አሁን ላይ ቁጥራቸው ተመናምኖ አንድ እድሜ ጠገብ አንበሳ ብቻ ቀርቶታል።

የአዲስ ዙ ፓርክ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ተስፋ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በግቢው የነበሩ አንበሶች ቁጥር ሊመናመን የቻለው አንበሶቹ በመዲናዋ በሚገኙ ሌሎች ፓርኮች በመዘዋወራቸው ነው።

ከግቢው አንበሶች መካከል አራቱ በቅርቡ ተመርቆ  ለአገልግሎት ክፍት ወደሆነው የፒኮክ መናፈሻ አዲስ ዙ ፓርክ መዘዋወራቸውን ገልፀዋል።

“ሌሎች ሶስት አንበሶች ደግሞ ወደ አንድነት ፓርክ ተዘዋውረዋል” ብለዋል።

አንበሶቹ የተዘዋወሩት ፓርኮቹ ለአንበሳ ተፈጥሯዊ ባህሪ ምቹ ሆነው በመገንባታቸው እንደሆነም አብራርተዋል።

ወደ ፓርኮች ከተዘዋወሩት አንበሳዎች መካከል አንዱ በእድሜ መግፋት ምክንያት መሞቱንም ጠቁመዋል።

አቶ ተስፋ ዋቅጅራ ተጨማሪ አንበሶችን በማዕከሉ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንበሳ ለማስመጣት እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን ተናግረዋል። 

በዚህም ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በማዕከሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።