በክልሉ ለሰላም መስፈንና ልማት መጠናከር በልዩ ትኩረት ይሰራል---የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር

78

አሶሳ ፤ሐምሌ 16 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ሰላምን ለማስፈንና ለልማት መጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ከ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ፤በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የልማት ሥራዎችን በስፋት ለማከናወን ይሰራል።

ህብረተሰቡን በማስተባበር በተለይ የመተከል እና ካማሽ ዞኖችን የቀደመ ሠላም ማስመለስ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ለምክር ቤቱ  አብራርተዋል።

ግብርናውን ማዘመን ሌላው የበጀት ዓመቱ የክልሉ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

"ለእዚህም በዘርፉ የተሠማሩ ኢንቨስተሮችን ከአርሶ አደሩ ጋር በማስተሳሰር ቴክኖሎጂን የማሸጋገር ሥራ ይሰራል" ብለዋል።  

በተጨማሪም የብድር ገንዘብ በስፋት በማቅረብ የህብረተቡን ኑሮ መቀየር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

"አሁን ባለው ሁኔታ ለክልሉ ህዝብ ሠላም ከጸደቀው በጀት በላይ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ  የምክር ቤቱ አባል አቶ ሰይፈዲን ሃሩን  ናቸው፡፡

የክልሉ ማዕድን ልማት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ "በሀብቱ በሚገባ ለመጠቀም የክልሉ አስፈጻሚው አካል ሠላምን ዘላቂ ማድረግ ዋነኛ ትኩረቱ እንዲሆን እንሰራለን" ብለዋል።

የመንገድ እጦት የክልሉ ሌላው ችግር መሆኑንና በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው፤ የክልሉ ህዝብ የተፈጥሮ ሃብቱን ተጠቅሞ ከድህነት እንዲላቀቅ የሥራ ባህሉን የማዳበር ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ፤  ምክር ቤቱ ለ2014 በጀት ዓመት የክልሉ በጀት 5 ቢሊዮን 890 ሚሊዮን 442 ሺህ ብር ማጽደቁን አስታውቀዋል፡፡

ከበጀቱ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር  የሚሆነው ከፌደራል መንግስት በድጎማ የሚገኝ ሲሆን ቀሪው ከክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ፣ ከእርዳታ እና ሌሎች የገቢ ምንጮች እንደሚሸፈን ተመልክቷል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት  ማምሻውን በአሶሳ ወረዳ ባሮ ቀበሌ ተገኝተው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም