የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለ”ህልውና ዘመቻ” ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

816

እንጅባራ፤ ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለ”ህልውና ዘመቻ” ባዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገልጿል።

የሀገርን ህልውና እያስጠበቀ ላለው ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማሰባሰብ በአማራ ክልል የ“ህልውና ዘመቻ” የሚል የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ 278 ሚሊዮን ብር በጥሬ እና በዓይነት በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል። 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የድጋፍ አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንግዳ ዳኛው እንዳመለከቱት፤ ህዝብን ከአሸባሪው ህወሓት ለመጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ መደገፍ አለበት።

እስካሁንም አርሶ አደሩንና የንግዱን ማህበረሰብ ብቻ በማነቃነቅ 17 ሚሊዮን 407 ሺህ ብር ድጋፍ መሰብሰቡን አስታውቀዋል። 

በተጨማሪም በዞኑ ከሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ በመወሰናቸው 118 ሚሊዮን 562 ሺህ ብር እንደሚሰበሰብም ነው ሰብሳቢው ያስረዱት።

እስካሁንም 515 ኩንታል በቆሎ፣ በሶ፣ ቆሎ፣ የእንጀራ ድርቆሽ፣ ዳቦ ቆሎ፣ የጤፍ ዱቄትና በርበሬ እንዲሁም 1ሺህ 800 ደርዘን ባለ 2 ሊትር ውሃ ተዘጋጅቶ መላኩን አስታውሰዋል። 

“የታቀደውን ድጋፍ ለማሰባሰብ እስከ ቀበሌ ድረስ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ አርሶ አደሩን፣ የንግዱን ማህበረሰብና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማነቃነቅ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል። 

የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ አቶ አምሣሉ የኔት ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ የሚውል 70 ሺህ ብር መለገሳቸውን ገልጸዋል።

የሀገር ህልውናና አንድነት ተጠብቆ ሰላም ካልሰፈነ እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት እንደማይቻል ጠቅሰው፤ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲሚቀጥምሉ አስታውቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ትንኮሳ የንግዱን ዘርፍና የባለሀብቱን እንቅስቃሴ ስለሚጎዳ ችግሩን ለማስወገድ ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ጁንታው በስልጣን ዘመኑ ታሪካችንን በሴራ ለማጥፋት ከሠራው ሥራ አንፃር የወር ደመወዝ መለገስ ያንሰናል” ያሉት ደግሞ በመንግስት ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ ወርቁ ናቸው።

የድጋፍ አሰባሰቡን ለማሳካት የዞኑ የባህል ቡድን በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በመዘዋወር ህዝቡን ለማነቃነቅና ድጋፍ ለማሰባሰብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱም ታውቋል።