በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአንድ ቀን ከ30 ሺህ በላይ ችግኝ ተተከለ

113

ጎንደር፤ ሐምሌ 16/2013 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ከ30 ሺህ በላይ ሃገር በቀል ችግኝ ትናንት መተከሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የችግኝ ተከላው የተካሄደው የፓርኩ ክልል በሆነው ''ቡይት ራስ'' በተባለው ስፍራ በአንድ ቀን  ነው፡፡

በችግኝ ተከላው የፓርኩ ስካውቶችና ሰራተኞች፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማህብረሰብ፣፤ የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ወጣቶችና ሴቶች ሊግ አባላት ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተተከለው ችግኝ የፓርኩን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ የሚያግዙ የኮሶ ፣ ወይራ፣ ጽድና ሌሎች ሃገር በቀል የዘፍ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በፓርኩ ውስጥ በዘንድሮ ክረምት የደን መራቆት በሚስተዋልባቸው ቦታዎች 20 ሄክታር የሚሸፍን የደን ልማት ስራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት አጋጥሞ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ደርሶበት የነበረው 1ሺ ሄክታር የጓሳ ሳርና የቁጥቋጦ ዛፍ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ማገገሙን  አስታውቀዋል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህልድርጅት /ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም