በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ የታተመው የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ተመረቀ

167

ሐምሌ 15/2013( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ የታተመው የቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ 'ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ' የተሰኘው ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ተመረቀ።

በደርግ ዘመነ መንግሥት ከደርግ አባልነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ብርሃኑ ባይህ ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ተጠልለው 30 ዓመታት ቆይተዋል።

ከ30 ዓመት በኋላም መንግሥት በሰጠው የምህረት ውሳኔ ከኤምባሲ ጥገኝነት በወጡበት በዚህ ዓመት 699 ገጾች ያሉት ግለ-ታሪካቸው 'ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ' በሚል ርዕስ ለሕትመት በቅቷል።

የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ስምንተኛው የሕትመት ውጤት የሆነው ይህ ግለ-ታሪክ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የባለታሪኩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ በመሥሪያ ቤቱ አዳራሽ ተመርቋል።

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በአጭር ጊዜ የተቋቋመው የአካዳሚው ፕሬስ ሳይንስና ሳይንስ ነክ እውቀቶች በቀላል ዋጋ ለህዝብ ለማድረስ ተልዕኮ ይዞ ትርፍ የማያገኝባቸው የሕትመት ውጤቶችን እያወጣ ይገኛል።

ስምንተኛ የሕትመት ውጤት የሆነው የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ መጽሐፍ ረጅም ጊዜ የወሰደ፣ በርካታ አርታኢያን የተሳተፉበት "የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የአገርን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ አሳትሟል" ነው ያሉት።

የመጽሐፉን ረቂቅ በመቀበል ወደ አካዳሚው ፕሬስ የወሰዱትና ተገቢው አርትኦት ተሰርቶለት ተከታተትለው ለሕትመት እንዲበቃ ያደረጉት የባለታሪኩ የቅርብ ወዳጅ የስነ-ሕይወት ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ናቸው።

ፕሮፌሰር ሽብሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከባለታሪኩ ብርሃኑ ባይህ ጋር በ1942 ዓ.ም የልጅነት ጊዜ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ውድቀት ድረስ ቅርብ ወዳጅነት ነበራቸው።

ባለታሪኩ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ ከገቡ በኋላ ግን ለ20 ዓመታት ሳይገናኙ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጠየቅ እድል ባገኙ ጊዜ የባለታሪኩን ረቂቅ ጽሑፍ በመቀበል ለህትመት ሲዘጋጅ 2 ሺህ 200 ገጾች እንደነበር ገልጸዋል።

ነገር ግን አካዳሚው ፕሬስ የሕትመት ሕግ ጋር ተያይዞ ከብዙ ምክክርና አርትኦት በኋላ የሚቀነሱ ታሪኮች ተቀንሰው በ699 ገጾች ተቀንብቦ እንዲታተም መደረጉን አውስተዋል።

በመጽሃፉ ይዘት ላይ ትንታኔ ያቀረቡት በቀድሞው መንግሥት ትምህርት ሚኒስትር የነበሩትና የአካዳሚ ፕሬሱ የህትመት ኮሚቴ አባል ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ናቸው።

'መጽሐፉ የግለሰብ ሳይሆን የአገር ታሪክ የያዘ ነው' ያሉት ዶክተር ያየህይራድ፤ ደራሲው የማስታወስ ችሎታ፣ አብዮተኝነትና የአቋም ሰውነት ጎልቶ ይታይባቸዋል ብለዋል።

የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ከደርግ ዘመን ባለሥልጣናት ውሳኔዎችን ለአብነትም የ60ዎቹ የዘውዳዊ ሥርዓት ባለሥልጣናት ግድያ በመቃወም የህግና የመርህ ሰው መሆናቸውን በይፋ ያሳዩ ሰው እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከልጅነት እስከ እውቀት ያለፉበትን ቦታና ሁኔት በዝርዝር መጻፋቸው ለቀጣይ ትውልድ ጠቃሚ ቅርስ ነው ብለውታል።

በተለይም የደርግን ዘመን አሠራር ግብታዊነትና ፈተናዎች፣ ስለ60ዎቹና ሌሎች ባለሥልጣናት ግድያ፣ የኦጋዴን፣ የኤርትራ ጉዳይ እና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር የተጻፉና ለተመራማሪዎች ግብዓትነት የሚውሉ ጠቃሚ ይዘቶች እንደሆኑ አንስተዋል።

በወታደርነት፣ በጦር መኮንንነትና በህግ ባለሙያነት የሰሩት ባለታሪኩ የወቅቱን ጉዳዮች ምስክር በመጻፋቸውና መጽሐፋቸው በርካታ ሐሳብ ቀስቃሽ በመሆኑ ሁሉም ሊያነበውና የታሪክ ባለሙያዎችም ሊያጠኑት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ መጽሐፍ ተመሳሳይነት ካላቸው ከሌሎች የደርግ ሥርዓት መንግስት ባለሥልጣናት ግለ-ታሪኮች በተለየ መንገድ የተብራራ ተረክ እንዳለው ተናግረዋል።

የ85 ዓመት እድሜ ባለጸጋው ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ በበኩላቸው፤ በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በነበሩበት ዓመታት በበርካታ ማስታወሻዎች የጻፉት ታሪካቸው ለህትመት መብቃቱን አመስግነው፤ ሂደቱም አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ገልጸዋል።

ለአብነት ለማሳየትም በተጠለሉበት ኤምባሲ ለ10 ዓመታት ማንም እንዲጠይቃቸው ባለመፈቀዱ በኋላም የተሰጣቸው ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር አማርኛ መጻፍ ባለመቻሉ በእንግሊዝኛ ተይበው በድጋሚ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉመው እንደጻፉት ተናግረዋል።

በመጽሐፉ ውስጥ በተለይም የኤምባሲ ቆይታቸውን በተመለከተ ያልተጻፋ ታሪኮች በኤምባሲው አብሯቸው ከነበሩት ከቀድሞው ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል ሀዲስ ተድላ ግለ-ታሪክ ጋር እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

'ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ' በሚል ርዕስ በ699 ገጾች የተቀነበበው የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ በ400 ብር ለገበያ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም