የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ቡድን ከቶኪዮ አየር ማረፊያ ወጥቶ ወደ ተመደበለት ቦታ ገብቷል - ዶክተር ሂሩት ካሳው

92

ሐምሌ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ቡድን ከቶኪዮ አየር ማረፊያ ወጥቶ ወደ ተመደበለት ቦታ መግባቱን የቡድኑ መሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

ነገ በሚጀመረው 32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ ወደ ጃፓን ያመራው የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ ትናንት ቶኪዮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደረስ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን አቀባበል እንደተረገላቸው ተገልጾ ነበር።

ይሁንና ሪፖርተር ጋዜጣ "ልዑኩ በተሳፈረበት አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ የሞዛምቢክና የናይጄሪያ ልዑካን አባላት የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው በምርመራ በመረጋገጡ ሁሉም ተሳፋሪ ከቶኪዮ አየር ማረፊያ እንዳይወጣ መደረጉን" ዛሬ ከሰዓታት በፊት ዘግቦ ነበር።

የልዑኩ መሪ ዶክተር ሂሩት ካሳው 30 የሚሆኑ አባላት የያዘው ቡድን በጃፓን ሰዓት አቆጣጠር 2 ሰዓት ከ30 ቶኪዮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጓዘበት አውሮፕላን ውስጥ የሞዛምፒክና የናይጄሪያ ልዑካን በትራንዚት መሳፈራቸውን ተናግረዋል።

በአየር ማረፊያው በተደረገው ምርመራ የናይጄሪያ ልዑክ አባል በኮሮናቫይረስ በመያዙ ሁሉም ተሳፋሪ ከአየር ማረፊያው እንዳይወጣ መደረጉን ገልጸዋል።

በአውሮፕላኑ የነበሩ ሁሉም ተሳፋሪዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ የደረገላቸው ሲሆን ናሙና ተወስዶ ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ ስድስት ሰዓት መፍጀቱንና በዚህም ምክንያት በአየር ማረፊያው መቆየት ግድ ማለቱን ተናግረዋል።

ረጅም ጊዜ የፈጀው የምርመራ ውጤት ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ ልዑክ አባላት ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ በጃፓን ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 9 ሰዓት በኋላ ከአየር ማረፊያው ወጥቶ ወደ ተመደበላቸው ቦታ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

ለልዑኩ አባላት የሚደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደሚቀጥልና ይህም በሁሉም የኦሊምፒክ ውድድሩ ተሳታፊዎች ተግባራዊ የሚሆን እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በውሃ ዋናና በወርልድ ቴኳንዶ የሚወዳዳሩት አትሌቶች ወደ ኦሊምፒክ መንደር መግባታቸውን፤ እንዲሁም የልዑኩ ሃላፊዎችና የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንደገቡም ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል።

በኦሊምፒክ የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ከነገ በስቲያ ወደ ቶኪዮ እንደሚያቀና አመልክተው አትሌቶች ተከፋፍለው የሚመጡት በጃፓን ባለው ሙቀት ምክንያትና በውድድሩ መርሃ ግብር ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል።

"በቀጣይ ወደ ቶኪዮ የሚመጡ የኢትዮጵያ ስፖርተኞች ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከትራንዚት ተሳፋሪዎች እንዳይመጡ ቢደረግ መልካም ነው" ብለዋል።

ነገ በሚጀመረው 32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ውሃ ዋናና ብስክሌት ስፖርቶች ትሳተፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም