የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ወድድር ይሳተፋል

1201

ሐምሌ 15/2013(ኢዜአ) በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ ለውድድሩ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የክለቡ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ገለጹ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

በውሳኔው መሰረት የመጀመሪያው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ በስድስት ዞኖች ተከፋፍሎ 34 ክለቦች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞን ከተደለደሉት ዞኖች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በዚህ ዞን ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብን ጨምሮ ዘጠኝ ክለቦች ይሳተፋሉ።

የዞኑ የማጣሪያ ውድድር በኬንያ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 9 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ ነው።

ንግድ ባንክ ለውድድሩ ከሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ የስፖርት ሜዳ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሚገኝ የክለቡ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ክለቡ ወደ ልምምድ ሲገባ 26 ተጫዎቾችን ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ አራት ተጫዋቾች በመጎዳታቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት በ22 ተጫዋቾች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለማጣሪያ ጨዋታው ክለቡ ከኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንና ከኢትዮጵያ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ማድረጉን አመልክተዋል።

በቀጣይም በአገር ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ሁለት ተጨማሪ ጨዋታ እንደሚያደርግ ነው አሰልጣኝ ብርሃኑ የገለጹት።

የማጣሪያ ውድድሩ በሐምሌ 2013 ዓ.ም ይካሄዳል በተባለበት ጊዜና ክለቡ ዝግጅት በጀመረበት መሐል የ15 ቀን አጭር ጊዜ በመኖሩ በአፍሪካ ከሚገኙ ክለቦች የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አልታሰበበትም፤ ያም ሆኖ ግን ውድድሩ እንዲራዘም መወሰኑን አስታውሰዋል።

የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከተጠናቀቀ አራት ወር ማስቆጠሩን አመልክተው፤ ይሄም ተጫዋቾቹ በነዚህ ጊዜ ውስጥ እረፍት ላይ በመቆየታቸው ተጫዋቾች ያላቸውን የውድድር አቋም ለመመለስ ፈታኝ አድርጎት እንደነበር አስልጣኝ ብርሃኑ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በተደረገው ልምምድና የአቋመ ፍተሻ ተጫዋቾቹ ዝግጁነታቸው ላይ ለውጥ እንደታየበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በማጣሪያው ውድድር በምድብ ሁለት ከደቡብ ሱዳን ዬይ ጆን ስታርስና ከዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽንስ ጋር ተደልድሏል።

“በቂ ባይሆንም ሁለቱ ክለቦች ያላቸውን ወቅታዊ አቋም ለማወቅ የተለያዩ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እየተሞከርን ነው” ብለዋል።

እንደአሰልጣኝ ብርሃኑ ገለጻ፤ የንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ የማጣሪያ ውድድሩ የሚያደርገው አሸንፎ ዞኑን ለመወከል ነው።

ለዚህም ክለቡ ጠንክሮ ከመስራቱ በተጨማሪ የቡድኑ መንፈስም ጥሩ የሚባል እንደሆነም ገልጸዋል።

ክለቡ በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚያስችለውን የክለብ ፈቃድ (ላይሰንስ) ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ማግኘቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ  21 ተጫዋቾችና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኬንያ እንደሚያቀና አሰልጣኝ ብርሃኑ ተናግረዋል።

በስድስት ዞኖች በሚካሄደው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ በእያንዳንዱ ዞን አሸናፊ የሚሆነው ክለብ በቀጣይ ሲገለጽ በግብጽ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2021 በሚካሄደው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናል።

ከስድስቱ ክለቦች በተጨማሪ አስተናጋጇ አገር ግብጽ በአንድ ክለብ የምትወከል ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2018 በጋና አስተናጋጅነት በተካሄደው 11ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ናይጄሪያ አንድ ክለብ እንድትወክል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) መወሰኑ የሚታወስ ነው።