በአማራ ክልል የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተጀመረ

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 15/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ሶስተኛው ዙር የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት 248 ሚሊዮን ችግኝ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለመትከል መረሃ ግብሩ ዛሬ ተጀመረ።
''ኢትዮጰያን እናልብሳት'' መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር የተጀመረው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፣ አርቲስት ስለሺ ደምሴ/ጋሽ አበራ ሞላ/ን ጨምሮ የተለያዩ የክልል የስራ ሃላፊዎችነና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በቤዛዊት ተራራ ላይ ነው።
ዛሬ የተጀመረው የችግኝ ተከላው መረሃ ግብር በሁሉም ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ተለይቶ በተዘጋጀ 24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ገልጸዋል።
በተከላውም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የደንና የፍራፍሬ ችግኞች እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመረሃ ግብሩ ከ4 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ እንደሚሳተፍ የሚጠበቅ መሆኑን ዶክተር መለስ አመልክተው፤ በየአካባቢው ይህን የሚመሩ አደረጃጀቶች ቀደም ብለው መዋቀራቸውን አስረድተዋል።
ዘንድሮ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ እና መደበኛው መረሃ ግብር 2 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በአንድ ጀምበር በተካሄደ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ከተተከለው190 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ህብረተሰቡ ባደረገው እንክብካቤ 78 በመቶ ማጽደቅ መቻሉም ተመልክቷል።