ኮቪድ-19 ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ወላጅ አልባ እድርጓል - ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19 ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ወላጅ አልባ እድርጓል - ጥናት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 14/2013 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ወላጅ አልባ ማድረጉን ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ በአለም አቀፍ ጥምረት በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል መሪነት በ21 የአለም አገሮች ላይ የተካሄደ ነው።
ወረርሽኙ በተከሰተባቸው የመጀመሪያዎቹ 14 ወራት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህጻናት ወላጆቻቸውንና የቅርብ ጠባቂዎቻቸውን አጥተዋል።
በጥናቱ በተካተቱ 21 አገሮች ውስጥ ከአንድ ሺህ ህጻናት ውስጥ ከሁለት በላይ የሚሆኑት ከኮቪድ ጋር በተገናኘ ወላጆቻቸውን እንዳጡ ተመላክቷል።
ችግሩን የከፋ የሚያደርገው 23 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት በአባት ወይንም በእናት ብቻ ያደጉ መሆናቸው ነው ።
ተጎጂዎቹ ወላጅ ካላቸው ህጻናት ጋር ሲነጻጸር ለጾታዊ ጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውም ጨምሯል።
ወረርሽኙ ከተገለጸው ቁጥር በላይ ህጻናትን ወላጅ አልባ እንዳያደርግ አስቸኳይና ፍትሃዊ የክትባት ተደራሽነትን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመክሯል።
በተጨማሪም ወላጆቻቸውንና የቅርብ ጠባቂዎቻቸውን በወረርሽኙ ያጡ ህጻናት ለመገለልና ጥቃት እንዲሁም ምጣኔ ሃብት ጫና ጉዳቶች እንዳይዳረጉ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህጻናት ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
ጥናቱ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ 2020 የተደረገ ሲሆን፤ በመጋቢት መጨረሻ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት 1 ነጥብ 34 ሚሊዮን ነበር።
በሚያዝያ መጨረሻ በ220 ሺህ በመጨመር 1 ነጥብ 56 መድረሱን በማሳየት አሳሳቢነቱን አስቀምጧል።
አሁንም ድረስ በዓለም ላይ የበርካታ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ወረርሽኙ ህጻናትንም ያለ ወላጅ እያስቀረ በመሆኑ በጤና ባለሙያ የሚመከሩ የመከላከያ መንገዶችን አዘውትሮ መተግበር እንደሚገባ ተመክሯል።
እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2019 መነሻውን ቻይና ያደረገው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፍጥነት ዓለምን በማዳረስ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ሲዳርግ፤ ከ192 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።