በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የህብረተሰቡን ችግሮች በሚያቃልሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው-ጽህፈት ቤቱ

82

ፍቼ ሐምሌ14/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የህብረተሰቡን ችግሮች በሚያቃልሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች 277ሺህ 803 የሚጠጉ ወጣቶችን ያሳተፈ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተካሄደ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ የወጣቶችና በጐ አድራጐት ቡድን መሪ ወይዘሮ ስኳሬ በላቸው እንደገለጹት በጐ አድራጊ ወጣቶቹ ለሁለት ወራት በሚያከናውኗቸው በአረጋውያን ቤት ጥገና፣ በግብርና፣ በደም ልገሳ፣ በትራፊክ ደህንነት፣ በኤች አይ ቪ ኤድስና የኮቪድ 19 መከላከል፣ በማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ተግባራት ተሰማርተዋል።

በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው 10 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ስራም እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በጐ ፍቃደኛ ወጣቶቹ በሚያከናውኑት ስራ ሌሎች ወጣቶች ጥሩ አርአያ ከመሆን ባሻገር ከአንድ ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚሆን አመልክተዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል በኩዩ ወረዳ በብሪቲ ቀበሌ በግብርና ሙያ አርሶ አደሩን እያገዘ የሚገኘው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ጥላሁን ካባ የትውልድ መንደሩ የሚስተዋሉ የህብረተሰብ ችግሮችን ለማቃለል በበጎፍቃድ አገልግሎት መሰማራቱን ገልጻል።

በወረዳው በሊበን ቀበሌ በችግኝ ተከላና ጽዳት ሥራ የተሰማራው የኮሌጅ አንደኛ ዓመት ተማሪ ባይሳ ወርቁ በአካባቢው የሚስተዋለውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የጽዳት ጉድለት በሚያሻሽሉ ስራዎች ላይ ግንዛቤ በመስጠትና በጉልበትም በመርዳት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም ወገናቸውን ለመርዳት ቢነሱ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ተናግሮ በተለይ አርሶአደሮች ዘመናዊ አሰራርን እንዲለማመዱ ያለውን ተሞክሮ እያካፈለ መሆኑን ገልጿል።

“የተቸገረ መርዳት እርካታ ይሰጠኛል” ያለችው በፍቼ ከተማ በቀበሌ 04 ነዋሪ ወጣት ትንሳኤ በቀለ  ሌሎች ወጣቶችም በአልባሌ ስፍራ ጊዜ ከማሳለፍ ተቆጥበው ችግር ውስጥ ያለውን ወገናቸውን ባላቸው እውቀትና ጉልበት ቢረዱ የራሳቸውም ሆነ የአካባቢያቸው የኑሮ ሁኔታ እንደሚለወጥ ተናግራለች።

በተለይ በኑሮ ዘዴ፣ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ ህብረተሰቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን ግንዛቤ ያላቸው ወጣቶች በሀላፊነት ቢሰሩ ሀገሪቱ ለተያያዘችው ሁለገብ ለውጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክታለች፡፡

በፍቼ ከተማ እያገለገለ ያለው የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ወጣት ብሩክ ዘውዴ  የተደራጁ  ክበባትን በእውቀትና ክህሎት ከማጠናከር በተጨማሪ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ የበኩሉን አያበረከተ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም