የግድቡ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የዲፕሎማሲና የዜጎች የተባበረ አንድነት ውጤት ነው —የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

955

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 14/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቅ የዲፕሎማሲና የዜጎች የተባበረ አንድነት ውጤት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባው  የውሃ ሙሌቱ በድል  የመጠናቀቅ  ሚስጥር የመንግስት   ቁርጠኛ  አቋም ፣ በአለም አደባባይ የተካሄደው ዲፕሎማሲ ፣ በሀገርና   ውጭ   የሚኖሩ ዜጎች  የተባበረ የአንድነት ድል ነው ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደርና በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪው በተገኘው ድል ሳይዘናጉ ግድቡ እስከመጨረሻ ተጠናቆ የሚፈለገውን አገልግሎት እስኪሰጥ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ የማስተባበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምልክትና ማንነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ  መግባቱ ይህን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር  አቶ አህመድ  ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥና ከፍታዋን ለማብሰር ዜጎች አሁንም አንድነታቸውን ከማንኛውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ለሀገርና ብሔራዊ አጀንዳዎች ስኬት መረባረብ ነው ያሉት፡፡

የሀገሪቱን ሰላምና ዕድገት ለማደናቀፍና ጫና ለመፍጠር የሚከናወኑ አጥፊ ተግባራትን  በአንድነት መመከት የሚቻለው ልዩነትን ወደ ጎን በመተው  ከምንም ነገር በላይ ሀገርን  በማስቀደም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መገባደዱን ይፋ የተደረገው   ሐምሌ12/2013ዓ.ም እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።