ኢትዮጵያን በኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች መምረጫ ውድድር በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል

75

ሐምሌ 14/2013 (ኢዜአ) በኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር በቀጣዩ ሳምንት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ሁለተኛው የኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ ከነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

በቼስ ኦሊምፒያዱ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈውን ብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር በሁለት ዘርፎች እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ማጣሪያው ብሊትዝና ራፒድ በሚል ተከፋፍሎ ይካሄዳል፤ ራፒድ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሁም ብሊትዝ ሐምሌ 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም ይከናወናል።

ራፒድ በሚል የሚጠራው የቼስ ጨዋታ 15 ደቂቃ የሚቆይ እንደሆነና ብሊትዝ በአምስት ደቂቃ ውስጥ የሚጠናቀቅ የጨዋታ አይነት መሆኑን አቶ ሰይፈ አመልክተዋል።

በማጣሪያው ውድድር መሳተፍ የሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች የመመዝገቢያ ጊዜ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።

በውድድሩ 300 የሚሆኑ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ ሰይፈ በወንድ ሶስት በሴት ሶስት በድምሩ ስድስት ተወዳዳሪዎች ከውድድሩ ይመረጣሉ ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ከተሳታፊዎች መካከል በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ተወዳዳሪዎች ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች መሆን እንዳለባቸው አስቀምጧል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች በወንድና በሴት አንድ አንድ ተወዳዳሪ እንደምታሳትፍ አቶ ሰይፈ ገልጸዋል።

እ.አ.አ 2020 በሩሲያ አስተናጋጅነት 44ኛው የቼስ ኦሊምፒያድ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ማራዘሙ የሚታወስ ነው።

ይሁንና ፌዴሬሽኑ በአካል የሚካሄደው ውድድር እስከሚጀመር ድረስ ውድደሩን ለማስቀጠል የኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ እ.አ.አ 2020 ለመጀመሪያ ጊዜ አካሄዷል።

በኦሊምፒያዱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ163 ብሔራዊ ቡድኖች የተወጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል።

በሁለቱም ጾታዎች ሩሲያና ሕንድ ለፍጻሜ ቢደርሱም በጨዋታው ወቅት ባጋጠመ የሰርቨር ብልሽት ምክንያት ሕንድና ሩሲያ የውድድሩ የጋራ አሸናፊ በሚል የወርቅ ሜዳሊያ እንዲያገኙ መደረጉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በቼስ ኦሊምፒያዱ በተመሳሳይ በሶስት ወንድና ሴት ተወዳዳሪዎች ተወክላ የተሳተፈች ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ ከነበሩበት ምድብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻሉም።

የሁለተኛው የኦንላንይን ቼስ ኦሊምፒያድ ልክ እንደ መጀመሪያው ውድድር በChess.com ሰርቨር አማካኝነት የሚካሄድ ነው።

የቼስ ኦሊምፒያድ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን አማካኝነት እ.አ.አ ከ1927 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም