በኮቪድ-19 ሕክምና ሕዝባቸውን በፍጹም ሰብዓዊነትና ርህራሄ ለሚያገለግሉ ባለሙያዎች ክብር ይገባል...ዶክተር ሊያ ታደሠ - ኢዜአ አማርኛ
በኮቪድ-19 ሕክምና ሕዝባቸውን በፍጹም ሰብዓዊነትና ርህራሄ ለሚያገለግሉ ባለሙያዎች ክብር ይገባል...ዶክተር ሊያ ታደሠ

አዲስ አበባ: ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከሕክምናው ጎን ለጎን በፍጹም ሰብዓዊነትና ርህራሄ ሕዝባቸውን በማገልገል ላይ ለሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ክብርና አድናቆት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ፡፡
በሚሊኒየም የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ለሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችና ለአጋር አካላት የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
ለባለሙያዎቹ እውቅና የሰጡት ዶክተር ሊያ ታደሠ ባለሙያዎቹ የበርካቶችን ሕይወት ለማትረፍ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮቪድ-19 በተፈራው ልክ በአገሪቷ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የእነኚህ ባለሙያዎች ሚና ጉልህ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም በሚሊኒየም የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል የሚሰሩ ባለሙያዎች ከሕክምና ሙያቸው ጎን ለጎን በፍጹም ሰብዓዊነትና ርህራሄ ሕዝባቸውን በማገልገል ላይ በመሆናቸው ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
ወረርሽኙ ከአገሪቷ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠፋ ድረስ የተለመደውን ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን በመጠበቅ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"ቀጣዩን ጊዜም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገረዋለን"ያሉት ዶክተር ሊያ ለባለሙያዎቹ አስፈላጊው ሁሉ በመንግስት እንደሚሟላላቸው ገልጸዋል፡፡

የሚሊኒየም ኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ የሕክምና ሙያ ለእውቅናና ሽልማት ሳይሆን ሰብዓዊነትን ማዕከል በማድረግ የሚሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ባለሙያዎቹ ኮቪድን ለመከላከልና ለማከም ሙያዊ ስነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ ከፍተኛ ተጋድሎ በመፈጸማቸው እውቅናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
ይህ እውቅናና ምስጋና በቀጣይም ሕዝብን ለማገልገል ሞራል እንደሚሆን አክለዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሕክምና ባለሙያዎችም ለረዥም ጊዜ ያለ እረፍት በመስራት ሕዝባቸውን በማገልገላቸውና በዚህም እውቅና ስላገኙ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
እውቅናው በቀጣይም ለተሻለ ሙያና ሃላፊነት የሚያነሳሳቸው እንደሆነም ነው የገለጹት።
የጤና ሚኒስቴር ይህ ሳምንት "የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች ሳምንት" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበርና ለባለሙያዎችም እውቅና እንደሚሰጥ መግለጹ ይታወቃል፡፡