የኢትዮጵያ ለሴቶችና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው – የቡርኪናፋሶ ልዑካን ቡድን

703

ሀምሌ 13/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሴቶች እና ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው ሲል የቡርኪናፋሶ የልዑካን ቡድን ገለጸ።

የፌዴራል ስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን የአመራር አባላት ከቡርኪናፋሶ የልኡካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ ስራዎችና በዘርፉ አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች ላይ ገለጻና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የውጭ ኢንቨስትመንትና የግሉን ዘርፍ በዘላቂነት መደገፍ እንዲሁም የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የተመለከተ ገለጻም ለልዑካን ቡድኑ ተደርጓል።

የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን ቡድኑ የኢትዮጵያን የስራ እድል ፈጠራ ተሞክሮና ዘርፉ እየተከተለ ያለውን አጠቃላይ መዋቅራዊ አሰራር ልምድ ለመቅሰም መምጣቱን ገልጸዋል።

መድረኩ በስራ እድል ፈጠራ በተሻለ ሁኔታ ከሄዱት የተሻለ ተሞክሮ፤ በችግር ውስጥ ካሉት ደግሞ ችግሩን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት እንደሆነም አቶ ንጉሱ አብራርተዋል።

የልዑካን ቡድኑን የመሩት የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት የሰው ሀይል ልማት ልዩ አማካሪ ፕሮፌሰር ኒኮላስ ሜዳ ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ እያከናወነች ያለቸው ተግባር ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

የሴቶችና የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየተሰራ ያለውን ስራ መመልከት መቻላቸውንም ገልጸዋል።