ሕጻናትን ለተስፋቸው ተዋቸው

167

ሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የዛሬ ሕጻናት የነገ ብሩህ ተስፋ ናቸው። እነርሱ ከሌሉ ሊኖር የሚችል ነገር የለም። ሁሉም ከንቱ ይሆናል።

ሕጻናት በአካል ጎልብተው፣ በትምህርት እውቀት ታጥቀው፣ ዘመን መሻገር የሚያስችል ስንቅ ይዘው ካላደጉ የነገ ብሩህ ተስፋ መሆን አይችሉም። 

ዛሬ ላይ እጣ ፈንታቸውን ጉልበተኞች፣ የሥልጣን እንጂ የአገር ጉዳይ የማይታያቸው እኩዮች ከቀየሱት ብሩህ ተስፋ የሚባል ነገር አይኖራቸውም።

ሕጻናትን በግጭት ቀጣና ውስጥ አሰልፎ የጥይት እራት ማድረግ የአገርን መጻኢ እድል የጨለማ ጉዞ ውስጥ መክተት ነውና። 

ለዚህም ነው ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና የአፍሪካ ኅብረት በህጎቻቸው የህጻናትን ጉዳይ በማካተት ግዝፈት የሰጡት። ተግባራዊ ሲሆን ግን በተሰጠው ግዝፈትና ክብደት ልክ አይደለም።

ነገሩ የተቃውሞና የውግዘት ርእስ መሆኑ እንዲሁም በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ባይወሰን ኖሮ ሕጻናትን እንደ አሸባሪው ህወሓት በግጭት ቀጣና ዋና ተሳታፊ አድርጎ ይቅርና ወታደሮችን እንዲረዱ፣ እንዲላላኩ ያደረገ ሁሉ ዋጋ እንዲከፍል ይደረግ ነበር።

ህጉ የሚደነግገው ሕጻናትን ታሳቢ አድርጎ ነውና። 

በዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀፅ 1 ዕድሜን መሠረት ያደረገው ትርጉም፣ "ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው" እንደሆነ ይገልፃል፡፡ 

የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደህንነት ቻርተር አንቀፅ 2 "ለዚህ ቻርተር ዓላማ ሲባል ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው፡፡" ይላል፡፡ 

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 215 መሠረት ደግሞ አካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ጾታ ሳይለይ ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መብት ድንጋጌ አንቀጽ 33 ማንኛውም አካል ሕጻናት የአደንዛዠ እፅ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማንኛውንም አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊ፣ ማኅበራዊና ትምህርት ነክ የሆኑ እርምጃዎችን እንዲወሰዱ ያስገድዳል፡፡

አንቀጽ 38/1 ደግሞ ሕጻናት በጦር ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ መንግስታዊ የሆኑ አካላት ጥበቃ እንዲያደርጉ ያዛል፡፡ በዚህም 18 ዓመት ያልሞላቸውን ልጆች በወታደርነት መመልመል የማይቻል መሆኑን አስቀምጧል፡፡

ሕፃናትን ለጦርነት መጠቀም፣ መመልመል፣ ማሰልጠን ወዘተ…. እነዚህ ሁሉ በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትም ድርጊቱ በባህሪው ዓለምአቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ነው፡፡ 

እነዚህ ሁሉ ዓለምአቀፍ ድንጋጌዎች ባሉበት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ምናልባትም ዕድሜያቸው 14 እና 15 ዓመት የሚሆናቸውን በርካታ ሕፃናት ምንም በማያውቁት ጉዳይ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርጓል፡፡ 

በዚህ ሂደት የተሳተፉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የሕግ ተጠያቂነት ያለባቸው ሲሆን፤ ድርጊቱ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለምአቀፍ ሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለዚሁ ተግባሩ ሲል በቅርቡ በርካታ ኩንታል አደንዛዥ እፅ በተሽከርካሪ ጭኖ ከሁመራ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሊያስገባ ሲል መያዙና አደንዛዥ እፁ ካናቢስ የተሰኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለውን አደንዛዥ እፅ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ሕፃናት እንዲጠቀሙት በማድረግ ወደ ጦርነት እያስገባቸው መሆኑን እጃቸውን የሰጡ ምርኮኞች የተናገሩት ሃቅ ነው። 

ዘራፊው ቡድን ሕፃናትን ወደ ጦርነት ማስገባቱ ሳያንስ ሕፃናቱ ዓለም አቀፍ ወንጀል የሆነውን አደንዛዥ ዕፅ  እንዲጠቀሙ ማድረጉ ዓላማውን ለማስፈጸም ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል የሚያሳይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሕጻናትና ግጭትን በተመለከተ በትኩረት መስራት ከጀመረ ሶስት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በአፍሪካ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በቁጥር መቀነሱ ቢታወቅም ሕጻናትን ለውትድርና መመልመል ግን አሁንም ተጠናከሮ ቀጥሏል፡፡

እነዚህን ሕጻናት ከጦርነት እሳት መታደግ ቢገባም አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸውና የስልጣን ጥማት እንቅልፍ የነሳቸው ስግብግቦች ሕጻናቱን በጦርነት ነበልባል እያስፈጇቸው ይገኛሉ፡፡

በመላው አለም ከ250 ሺህ በላይ ሕጻናት ወታደሮች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ይህን እኩይ ተግባር የማስቆም ኃላፊነት ቢወድቅበትም በአህጉሪቱ ባሉ ራስ ወዳዶች ምክንያት ድካሙ ከንቱ ሆኖበታል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እ.አ.አ ከ1999 አንስቶ ሕጻናትና ጦርነትን በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በርካታ ድንጋጌዎችንም አውጥቷል፡፡

ምክር ቤቱ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ደህንነት መጠበቁን ለመከታተል እ.አ.አ 2005 ባወጣው ድንጋጌ ቁጥር 1612 በመታገዝ እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም አፍሪካ ውስጥ በሊቢያና አይቮሪኮስት በነበረው ግጭት በርካታ ሕጻናት ለጦርነት መሰለፋቸው የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው፡፡

በአገራችንም በትግራይ ክልል የመሸገው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በቅርቡ ለክፉ ዓላማው ማስፈጸሚያ ሕጻናትን ከእናቶቻቸው ጉያ በመንጠቅ በጦርነት ማሰለፉን ዓለም ታዝቧል፡፡ በታዘበው መጠን ምንም ለማለት አልሞከረም እንጂ!

የአፍሪካ ኅብረት ባለበት ከፍተኛ የሞራል ኃላፊነት ይህንኑ ሕጻናትን ወደ ጦርነት የመማገድ ተግባር ለማስቆም ማውገዝና ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ አቅሙንና የማስፈጸም ገደቡን በማስፋት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

ባለፉት ሶሰት አስርት ዓመታት የወጡ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በጦር መሳሪያ የተደገፉ ግጭቶች ታክቲካቸውንና ባህሪያቸውን ቀይረው ብቅ እያሉ ነው፡፡

ይህ አቀራረብ ሕጻናትን በእጅጉ ወደ ጦርነት እየማገዳቸው ሲሆን የጦርነቱ አቀጣጣዮች ደግሞ ሕጻናቱን፣ ራሳቸውንና ሌሎችን በቦምብ በማጥፋትና በሽብር ተግባር እንዲሳተፉ እያደረጓቸው ነው፡፡

በቅርቡ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የታየው ተግባር ይህንኑ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

በአፍሪካ የሕፃናት መብት ቢደነገግም በሚደንቅ ሁኔታ ተፈጻሚነቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ በተለይ ደግሞ በግጭት ወቅት የሕጻናትን መብቶች በማስጠበቅ ያለው ሪከርድ አነስተኛ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መብት ድንጋጌ እና በአፍሪካ ኅብረት የሕጻናት ቻርተር መሰረት የሕጻናት ደህንነት በተገቢው መንገድ መከበር አለበት፡፡

በኅብረቱ ቻርተር አንቀጽ 22 መንግስታትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ደንብ በማክበር በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ማናቸውም ሕጻናት በግጭቱ ተካፋይ እንዳይሆኑ ማረጋገጥም የሁሉም ግዴታ ነው፡፡

ጥረቱ እንዳለ ቢሆንም አሁንም በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በቻድ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በማሊ፣ በሶማሌ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ሕጻናትን ለጦርነት የማሰለፉ ተግባር መቀጠሉን በርካታ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

ሰሞኑን ደግሞ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ይህንኑ ተግባር በመከተል በርካታ ሕጻናትን በጦርነት እሳት እየማገዳቸው መሆኑን በአደባባይ አሳይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም