በዘንድሮ የአረንጋዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን ከ152 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክሏል-የአማራ ክልል ግብርና ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮ የአረንጋዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን ከ152 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክሏል-የአማራ ክልል ግብርና ቢሮው
ባህር ዳር ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ)በአማራ ክልል በዘንድሮ 3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ152 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተወካይ አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ በ“ኢትዮጵያን እናልብሳት” 3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 2 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሁሉም ዞኖች በተጀመረው መርሃ ግብሩ እስካሁን ከ152 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን አስታውቀዋል።
ዝናቡ ቀደም ብሎ መጣል በጀመረባቸው በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደርና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ተከላው ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተሳታፊ እንደሚሆን ጠቁመው እየተተከሉ ያሉት ችግኞች የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የህብረተሰቡን የችግኝ እንክብካቤ ባህል በማጎልበት የፅድቀት ምጣኔውን ከ78 ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አቶ እስመላለም ተናግረዋል።
በጋራ መጠቀሚያ መሬት ላይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባለፈው ሳምንት መጀመራቸውን የገለጡት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የሳርና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለቃ ማረው ባየ ናቸው።
በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ያላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች በተከላ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በጋራም ሆነ በግላቸው ለሚተክሏቸው ችግኞች አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ምርት መስጠት ባቆመ ሩብ ሄክታር መሬት ተክለው ካሳደጉት የባህር ዛፍ ተክል ሽያጭ ባለፈው ዓመት ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በወረዳው የማይነት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰንደቄ አወቀ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመሳተፍ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች እየቆፈሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በግማሽ ሄክታር መሬት የባህር ዛፍ፣ የቀርከሃና የጌሾ ችግኞች ተክለው በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ለጥቅም ከደረሰው ባህር ዛፍና ከጌሾ ሽያጭም ከ85 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውን ጠቁመው በቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በስፋት ለመትከል እቅድ እንዳላቸው አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅት ከተተከሉ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች 78 በመቶው መጽደቃቸን የቢሮው መረጃ ያመላክታል።