ህጻናት ልጆችን ከበሽታ ለመታደግ እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ ጡት ማጥባት ይገባቸዋል ተባለ

58
አዲስ አበባ ነሀሴ 1/2010 የስርዓተ-ምግብ መዛባት ህጻናት ልጆችን ለበሽታ እንዲጋለጡና የማሰብ አቅማቸውን ዝቅተኛ ስለሚያደርግ እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ ጡት ማጥባት እንደሚገባቸው ተገለጸ። የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት በኢትዮጵያ ለአስረኛ ጊዜ ''ጡት ማጥባት የህይወት መሰረት'' በሚል መሪ ሐሳብ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ሲከበር ቆይቷል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የመዝጊያ ስነ ስርዓቱን ዛሬ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን አክብሯል። በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የኒውትሪሽን ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ቢራራ መለስ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ እናቶች ጡት ያጠባሉ። ይሁንና ከእነዚህ ወስጥ አግባብነት ባለው መልኩ በወቅቱና በጊዜው ለልጆች ጡት የሚያጠቡ እናቶች 58 በመቶ ብቻ ናቸው። በመሆኑም ህጻናትን ከበሽታ ለመከላከል ስድስት ወራት እስኪሞላቸው ድረስ የእናት ጡትን ብቻ በአግባቡ ማጥባት ስለሚያስፈልግ እናቶች ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ህጻናት ሃኪሞች ማህበር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ቦጋለ ወርቁ እንዳሉት" ኢትዮጵያ በህጻናት ሞት ቀዳሚ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ ነች።" ለዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ህጻናት በቂ የእናት ጡት አለማግኘታቸው ሲሆን እናቶች ለልጆቻቸው በቂ የጡት ወተት መመገብ አለመቻልም እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል። የህክምና ባለሙያዎችም እናቶች በሚወልዱበት ወቅት ስለ እናት ጡት ወተት ጥቅም በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ  ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሴቭ ዘ ቺልድረን ተወካይ ወይዘሮ እስራኤል ሃይሉ እንደተናገሩት" የምግብ እጥረትና የተዛባ የአመጋገብ ስርዓት ህጻናት በቀላሉ ለበሽታ እንዲጋለጡና ያለ እድሜያቸው ህይወታቸው እንዲቀጠፍ ከማድረጉም በላይ አእምሮና አካላዊ እድገታቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖም ከፍተኛ ነው።" በዚህም ባለፉት አስርተ አመታት በምግብ እጥረትና አለመመጣጠን ችግር የሚጠቁ ህጻናትን ቁጥር ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች በተለይም የመቀንጨር ችግርን ከ58 በመቶ ወደ 38 በመቶ ለመቀነስ መቻሉን ተናግረዋል። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል በተለይም እናቶች የጡት ማጥባት ተግባርን በተገቢው መንገድ ማከናወን ይገባቸዋል ነው ያሉት። የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኤሪክ አሌይን፤ ድርጅቱ በጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። በተለይም የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ፣ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ለጤና ተቋማትም ሆነ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ብሎም ክትትልና ድጋፉን ለማጠናከር መሆኑንም ነው የጠቆሙት። በዓለም ላይ የእናት ጡትን በማጥባት ብቻ 800 ሺህ ህጻናትን ከሞትና ከተለያዩ በሽታዎች ማዳን እንደሚቻል መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም