በሦስት የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት መታየቱ ተገለጸ

80

ሐምሌ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በመሬት አስተዳዳር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ አሁንም ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ።

የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን 3ኛው አገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናትና የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የሙስና ሁኔታ በተመለከተ ጥናት አካሂዷል።

ጥናቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች ከተለያዩ የህይወት መስክ ላይ የሚገኙ 6 ሺህ 627 ሰዎችን አካቷል።

ጥናቱንም 'ፍሮንቴር' የተሰኘ የጥናት ተቋም 130 ባለሙያዎች መድቦ አካሂዶታል።  

የጥናቱ ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሃብታሙ ወንድሙ እንደተናገሩት፤ ጥናቱ በአገሪቷ አሁን ላይ ያለውን የሙስና ደረጃ አመለካከት አሳይቷል።

በዚህም መሰረት ሙስናን ማጥፋት ለእድገትና ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ በመሆኑ የሙስና መከላከል ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥናቱ መጠቆሙን ተናግረዋል።

የጥናቱ ውጤትም በአሁኑ ወቅት አገሪቷን ከሚፈትኑ ትላልቅ ችግሮች መካከል ሙስና በ3ኛ ደረጃ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይም ደግሞ በአገሪቷ በመሬት አስተዳዳር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት መኖሩንም ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች አካባቢም ታጋላጭነት መኖሩን ጠቁመዋል።

ስለዚህም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየስ እንደሚገባቸው ጥናቱ ማመልከቱን ነው የተናገሩት።

ድርጊቱን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በበኩላቸው "ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ወጥ ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው" ብለዋል።

የተዘጋጀው ፖሊሲ በተለያዩ መድረኮች በዘርፉ ባለሙያዎችና በሚመለከታቸው አካላት በሚሰጡ ግብዓቶች ከበለጸገ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ እንደሚላክ ገልጸዋል።

የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል የጥናቱን ውጤት እንደ ወሳኝ ግብዓትነት በመጠቀም ሙስና የመከላከል ሥራውን ለማጠናከር እንደሚረባረብ አቶ ወዶ አጦ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም