በፖለቲካው ያለንን ተሰሚነት በመጠቀም ወጣቶችን ለሰላምና ስራ እድል ፈጠራ እናነሳሳለን - አቶ ጀዋር መሐመድ

62
አዲስ አበባ ነሀሴ 1/2010 በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሰሚነትና እንደ ሚዲያ ሰው ያለባቸውን ኃላፊነት በመጠቀም ወጣቶችን ለሰላምና ስራ እድል ፈጠራ እንደሚያነሳሱ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ ገለጹ። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የስራ ኃላፊዎች ጋር በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና በዲያስፖራው ተሳትፎ ዙሪያ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ያለውን ተስፋ ሰጭ የፖለቲካ ለውጥ በመደገፍ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን መርጠዋል። ባለፉት ዓመታት የነበረው "የአፈናና የጭቆና ስርዓት ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን፣ አንድነት እንዲጎለብት እንዲሁም እድገት እንዲመዘገብ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል አቶ ጀዋር። ያለንን ተሰሚነት በመጠቀም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጰያውያንም እንዲሁም በአገር ውስጥ የለውጡ መሪ የነበሩ ወጣቶችን በስራ እድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር በንቃት እንዲያሳትፉ ግፊት እናደርጋለን ብለዋል። አቶ ጀዋር አክለውም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መረጋገጥ እንዲችል "አፋኝና ጨቋኝ የሆኑ ህጎችን ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ማንሳት ያስፈልጋልም" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ጉብኝታቸው "በ2012 'ነጻ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ይከናወናል' ብለው ቃል የገቡትንም ለመተግበር ገለልተኛ ተቋማት መጠናከር አለባቸው" ብለዋል። ገለልተኛ ተቋማት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል አቶ ጀዋር። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው የኦ ኤም ኤን የስራ ኃላፊዎች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ላሳዩት ፍላጎት ምስጋና አቅርበዋል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉ የለውጡ መሪ ወጣቶችን በአገር ግንባታ ላይ በንቃት ለማሳተፍ ሲያስተባብሩ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግም መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም