የአማራ እና የኦሮሚያ ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም፣ አብሮናትና ልማት ተባብረው እንደሚሰሩ ገለጹ

81

ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) በህውሃት በጥባጭ ቡድን የተጀመረውን ሀገረን የማፍረስ እኩይ ተግባር በጋራ በማክሸፍ ለአካበቢ ዘላቂ ሰላም፣ አብሮናትና ልማት ተባብረው እንደሚሰሩ የአማራ እና ኦሮሚያ ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቶቹ የህግ ማስከበር ስራውን ለመደገፍ የሚያስችል የጋራ መድረክ ለመፍጠር በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ በመገኘት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሄደዋል። 

በብልጽግና ፓርቲ  የሰሜን ሸዋ ዞን  ወጣቶች ሊግ ሃላፊ  አበባው መለሰ በመድረኩ እንዳለው፤ በቀደሙት ዓመታት ህውሃት የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር አልሞ ሲሰራ ኑሯል።

በተለይም ለዘመናት ተዋዶና ተዋልዶ በኖረው የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል መጥፎ ጠባሳ ለመጣል ቢጥርም በህዝቦች አርቆ አሳቢነት ሳይሳካለት መቅረቱን አውስቷል።

እኛ ወጣቶች ከአባቶቻችን የወረስነው ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን እንጂ ጥላቻን ያለመሆኑን ለመላው አለም ለማሳየት ከምስራቅ ሸዋና ከኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ  ወጣቶች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በጋራ ለመስራት ውይይት አድርገናል ብሏል።

እንዲሁም የአካባቢን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ዘላቂ ልማትና አብሮነትን ለማጠናከርም እርስ በእርስ መወያየት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መድረኩ መዘጋጀቱን አመላክቷል።

የሃገርን ህልውና እየተፈታተነ ያለውን የህውሃት ጁንታ ለመመከት በህግ ማስከበር ስራው ተባብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን የገለፀው  ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ሊግ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወጣት አዲናን ሀጂ ነው፡፡

የገጠመነን የጋራ ችግር በሃገር በቀል እውቀት ዘዴን ተጠቅመን ከመፍታት ባሻገር የጋራ ጠላት የሆነውን ህውሃትና ድህነትን ተባብረን በማሸነፍ ኢትዮጵያን ለማሻገር አበክረን እንሰራለን ብሏል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጠላት የሆነውን ጁንታውን ለመዋጋት ወጣቶች የጋራ አስተሳሰብና አንድነትን ለማጠናከር የጋራ መመድረኩ መዘጋጀቱ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው  ገልጿል።

ጁንታው በአማራ ህዝብ ላይ የጀመረው ጥላቻና ጦርነት ለመላው ኢትዮጵያዊንን ጭምር በመሆኑ አንድነታቸውን በማጠናከር የጁንታውን ሃይል ለመደምሰስ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም  አስታውቋል።

ህብረተሰቡን አስተባብረው ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግሯል።

የጣርማ በር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ የሺዳኛ ፈቄ ፤ ከጦርነት ውጭ በልማትና በሰላም መኖር ያልታደለው ጁንታው ሃገር ለማፈራረስ የከፈተብን ጦርነት እስከ መጨረሻው እልባት ለመስጠት የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የሁለቱ ክልሎች ወጣቶች የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ በማስቀጠል በሁሉም አካባቢዎች ቁርኝት መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የወረዳው ህዝብ  የመንግስት ጥሪ ተከትሎ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ በግንባር ላይ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የሁለቱ ክልልች ወጣቶችም በጣርማ በር ወረዳ የአንድነትና የወዳጅነት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማካሄዳቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የተተከሉት ችግኞች መጥፎ ጥላቻን በማስወገድ መልካም ፍሬ የምናፈራበትና የበለፀገችና በፍቅርና በሰላም የተሳሰረ ህዝብ ለመገንባት የሚበጅ ነው ብለዋል።

በችግኝ ተከላው ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን እና ምስራቅ ሸዋ ዞን እና ከአማራ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ 600 የሚደርሱ ወጣቶች ከ4 ሺህ በላይ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም