በምርጫ ወቅት ያነሳሁትን ፎቶ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለሌላ ዓላማ ያለአግባብ ተጠቅሞበታል - የኤፍፔው የካሜራ ባለሙያ

ሀምሌ 10/2013 (ኢዜአ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል "የትግራይ ተወላጆች ታሰሩ" በሚል ይዞት የወጣው ፎቶግራፍ "በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎችን ያነሳሁት ነው" ሲል የኤፍፒው የካሜራ ባለሙያ አማኑኤል ስለሺ ገለጸ።

የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ  ፎቶግራፈር አማኑኤል ስለሺ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተጠቀመው ፎቶ ፎቶግራፈር አማኑኤል ለምርጫ ዘገባ ወቅት ያነሳው ነው።

የኢዜአ ፖርተር ያነጋገረው የኤፍፒውን የፎቶ ግራፍ ባለሙያ አማኑኤል ስለሺ እንዳለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል "የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ ነው" በሚል የተጠቀመው ፎቶ "እኔ በምርጫ ወቅት ያነሳሁትን ፎቶ ነው" ብሏል።

ፎቶው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ወቅት በእርሱ የተነሳ መሆኑንም አረጋግጧል።

አማኑኤል ፎቶውን ያነሳው በአዲስ አበባ አዋሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉትን መሆኑንም ተናግሯል።

በእለቱ ከማለዳው 12 ሰዓት ላይ እንዳነሳው አስታውሶ፤ ፖሊስ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሚገቡ መራጮችን ሲፈትሽ በነበረበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል።

ሆኖም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው ሪፖርት ላይ ፎቶው ለራሱ በሚፈልገው መልክ ያለ አግባብ መጠቀሙ እንዳሳዘነው ገልጿል።

የፎቶውን አላማ በማይገልጽ መልኩ ማቅረብ ሙያዊ ስነ ምግባር የሚጥስ መሆኑን ጠቅሷል።

"የሚዲያ ተቋሙ ፎቶውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ላልተፈለገ ተግባር አውሎታል፤ ይሄም ሕዝብ ለሕዝብ ጋር የሚያቃቅር ድርጊት ነው" ሲል የፎቶ ባለሙያው የገለጸው።

"አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በፍጹም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እንዲቃቀር የማድረግ ፍላጎት የለውም" ነው ያለው ባለሙያው።

ከዚህ ቀደም አንዳንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ምንጭ ሳይጠቅሱ የኤፍፒን ፎቶ እንደ ራሳቸው አድርገው የመጠቀም አጋጣሚዎች እንደነበሩ ጠቁሞ፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊት ግን ከዚህ የተለየ ተግባር እንደሆነ ገልጿል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፎቶውን ካሰራጨባቸው አማራጮች ላይ እንዲያወርዱ በስልክ፣ በኢሜልና በሌሎች አማራጮች ቢጠየቅም ከተቋሙ እስካሁንም "ምንም ምላሽ" እንዳልተገኘ ገልጿል።

የኤፍፒ ፎቶዎችን የሚጠቀም ማንኛውም አካል የፎቶውን ባለቤት መጥቀስ እንዲሁም መቼና የት እንደነሳ መግለጽ እንዳለባትና ላልተፈለገ አላማ መጠቀም እንደሌለበትም አሳስቧል።

አንዳንድ የውጭ መገናኛ በዙሃን እንዲሁም ተቋማት ሚዛናዊ ያልሆናኑ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ምስል ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም