አሸባሪው ህወሃት በውጭ ሀገራት ተንታኞች ዕይታ

111

አብዱራህማን ናስር (ኢዜአ)

ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና ተንታኝ ጄፍ ፔርስ “ዓለም ወደ እብደት አምርቷል፤ በተግባር የሽብር ተግባራትን የሚፈጽምና መሠረተ ልማቶችን የሚያቀርበውን ለማጥፋት ብሎም ተጨማሪ ቦታዎችን ለመውረር እየዛተ የሚገኝ ድርጅት የስልክ እና መሰል አገልግሎቶች እንዲመለስለት ለመጠየቅ ምን መብት አለው? በማለት ይጠይቃሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር ሮበርት ጎዴክ ለኮንግረሱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ ምንም ለውጥ አላመጣም፤ እንደውም ሁኔታው እየተባባሰ ነው፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲሉ፤ መንግሥት የተኩስ አቁም ባወጀ በማግስቱ የአሸባሪው ቡድን አፈቀላጤ በአሶሾዬትድ ፕሬስ ላይ የትግራይን መሬት ሙሉ በሙሉ ከማስለቀቅ የሚገታቸው ነገር እንደሌለ እና አስፈላጊ ከሆነ ወደኤርትራም ሆነ ወደ አማራ ክልል እንደሚዘምቱ መግለጹን ግን ሁሉም ሰምቶ እንዳልሰማ መሆኑን ፀሐፊው ያነሳሉ።

ፀሐፊው በሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ የገባው የህወሓት ቡድን ምንም ጥፋት እንዳልፈጸመ የባይደን አስተዳደር እንዴት ዝም ብሎ ይመለከተዋል የሚል ጥያቄ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተወካዮች ቢቀርብላቸው መልስ የላቸውም ሲሉም ይገልጻሉ።  

የህወሓት የሽብር ቡድን ምእራባውያን ሚዲያዎችን ዳጎስ ባለ ገንዘብ እንደአሻንጉሊት እንዳደረጋቸው የሚገልጹት ጸሐፊው እንደ አሌክስ ዴዋል፣ ጄትል ትሮንቮል እና ማርቲን ፕላውት ያሉት አንዳንድ ተንታኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጩ መቆየታቸውን አብራርተዋል። ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ላወረንስ ፍሪማን “Horn of Africa Endangered by Untrue Media Attacks on Ethiopia” በሚል ርእስ ባወጡት ዘገባ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን በሚያሰራጩት ከእውነት የራቀ ዘገባ የአፍሪካ ቀንድ ለአደጋ መጋለጡን አብራርተዋል።

ጄትል ትሮንቮል ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል በተካሄደው ህገ-ወጥ ምርጫ ላይ ብቸኛ ዓለም አቀፍ ታዛቢ በመሆን ተገኝቶ ነበር። ይህ ግለሰብ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደብቆ ባስገባው የሳተላይት ስልክ ከሽብር ቡድኑ አመራሮች እና የጦር አዝማቾች ጋር በየቀኑ በሳተላይት ስልክ እንደሚገናኝ ጄፍ ፒርስ ጽፈዋል። ትሮንቮል ከህወሓት ቡድን ጋር በሳተላይት ስልክ እንደሚገናኝ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

ትሮንቮል ከሙያው ስነምግባር ጋር በሚቃረን መልኩ የአንድ ወገንን የተዛባ መረጃ ብቻ በየእለቱ በትዊተር ገጹ ላይ ከማሰራጨት በተጨማሪ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየቀረበ “ኢትዮጵያ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እየገባች ነው” በሚል ደጋግሞ ተናግሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የረሃብ አጀንዳ ማቀንቀን የእለት ተእለ ጉዳዩ አድርጎታል። መንግስት በወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ መሰረት የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል በወጣበት ወቅት ተሸንፎ እንደወጣ እንዲሁም መንግስት “እየተዳከመ” ነው በሚል በሀገሪቱ አመጽ ሊቀሰቀስ እንደሚችልም ጽፏል።

አሌክስ ዴዋል ከትግራይ ክልል የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በርካታ ጽሑፎችን ጽፏል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በቅርቡ “ጄኔራል ፃድቃን ከትግራይ ኃይሎች ጀርባ ያለው ሞተር” በሚል ርእስ ባስነበበው ዘገባ የቡድኑ ተዋጊዎች የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጥምር ኃይሎች በአሰደናቂ ሁኔታ ድል ማድረጋቸውን ገልጿል። “በጣም ጥቂቶች የጠበቁትን አስደናቂ ድል ነው የተጎናፀፈው፣ የኢትዮጵያ ጦርም ከፍተኛ መሰናክል ገጥሞታል” በማለት ነበር ትንታኔውን ያሰፈረው። አክሎም “በርካታ የጦር መሳሪያዎችን የያዘው የትግራይ መከላከያ ኃይል ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ተጣምሮ ከነበረው የኤርትራ ጦር ጋር ስለሚገጥም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰሜን ትግራይ መውጣት ወይም መዋጋት የሚለውን መወሰን አለባቸው፤ ምናልባት ሌላ ጦርነትም ይከሰታል” ሲል የቡድኑን ጀግንነትና ወደፊትም ማንም ሊቋቋመው የማይችል እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል።

እዚህ ላይ ሊታለፍ የማይገባው ነገር የትግራይ ክልል እንደማንኛውም ክልል ፖሊስ ወይም ልዩ ሃይል እንጂ መከላከያ ሰራዊት የለውም። ይህን እያወቁ ምእራባውያን ተንታኞች እና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው “የትግራይ መከላከያ ሠራዊት” በማለት በራሳቸው ህገ ወጥ እውቅና ሰጥተዋል። ይህም ምንም እንኳ ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን የሌለውን ገጽታ ለማላበስ ዓላማ ያለው ቢሆንም ቅጥፈታቸው ምን ያህል እንደደረሰ የሚያሳይ ነው።  

ማርቲን ፕላውት ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በየሰዓቱ በትዊተር ገጹ ላይ የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ከእውነታ የራቁ ናቸው። ግለሰቡ አንድም ቀን የፌዴራል መንግስቱ በክልሉ ባደረገው የህግ ማስከበር ተግባር ላይ ለህዝቡ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በበጎ መልኩ ሲያነሳ አልተሰማም፡፡ በቅርቡ በቲውተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ መንግስት የእርዳታ ድርጅቶች በቀጥታ በረራ እንደማይፈቅድ የወሰነውን መቃወሙን ያሳየው ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር እንደተጋጨች በመግለጽ ነበር። 

ማርቲን ፕላውት እንደ መሰሎቹ ሁሉ የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ በወጣበት ወቅት በሽንፈት እንደወጣ ሲተነትን ቆይቷል። ሰሞኑን ቡድኑ አላማጣን መቆጣጠሩን ማንም ሳይቀድመው ነበር የዘገበው። መንግስት የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ በገለጸበት ወቅት ደግሞ “በቱርክ መንግስት ድጋፍ ድሮኖች በአዲስ አበባ እየተሰሩ ነው” በሚል ሀሰተኛ ዘገባ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

እነዚህ የውጭ ተንታኞች የህወሃት ቡድን ያልማረከውን ሰራዊት እንደማረከ እንዲሁም የተፈጸሙ ወንጀሎች በሙሉ መንግስት ባሰማራቸው ሠራዊት የተፈጸሙ መሆናቸውን በአንፃሩ የህወሓት ቡድን ከደሙ ንፁሕ እንደሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት የተለያዩ ትንታኔዎችን ሰርተዋል። ቡድኑ የሰራቸውን የተቀነባበሩ የፎቶ እና የቪዲዮ ምስሎችን በማሰራጨት የተዛባ ምስል እንዲፈጠር አበክረው ሰርተዋል። አልተሳካላቸውም እንጂ የኢትዮጰያ ህዝብ እርስ በርስ እንዲከፋፈል በርካታ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። ግለሰቦቹ ራሳቸውን የሰላም አቀንቃኝ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ለዓለም ህጎች ተከራካሪ እንደሆኑ ቢናገሩም በተግባራቸው ግን አሸባሪውን በማበረታታት ሥራ ላይ ተጠምደዋል።

ጄፍ ፔርስ “Ethiopia: Mao, Mango and the Guerilla Playbook በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ላይ የሽብር ቡደኑ ንጹሃን ተማሪዎችን ሲገድል፣ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ መሰረተ-ልማቶችን ሲያወድም ዝምታን የመረጡት እነዚሁ ሰዎች የሽብር ቡደኑ የሚያሰማውን ጩኸት ብቻ እየተቀበሉ የሀሰተኛ መረጃ ማሽንነታቸውን ቀጥለውበታል ብለዋል። የሽብር ቡድኑ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ሳይሆን ቡድኑ ተፈጸመብኝ የሚላቸውን ብቻ በመያዝ እጃቸው ላይ በሚገኝ ስልክ የግል የማህበራዊ ትስስር ገጻቸውን በመጠቀም የፕሮፖጋንዳ ማሽን ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ጸሀፊው በቅርቡ የመከላከያ ሰራዊት የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሳኔን መነሻ በማድረግ ከትግራይ በወጣበት ወቅት የህወሃት የሽብር ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር አባላት የነበሩ ሰዎችን መግደሉን እያወቁ “ደግ አደረግህ” ከማለት ያልተናነሰ ዝምታን መርጠዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።  

ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡ በፎቶግራፍ አስደግፎ ባወጣው መረጃ ላይ የህወሓት ቡድን ህፃናትን መሳሪያ አስታጥቆ ማሰለፉን አስነብቧል። ኒዮርክ ታይምስ ይህን ዘገባ የሰራው ወጣቶች መነቃቃታቸውን በማሳየት አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ለማሞካሸት ነበር። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ህግ እና እኤአ ከ2002 ጀምሮ ኢትዮጵያም ፈርማ በተቀበለችው የዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ለውትድርና መመልመል እና በጦርነት ማሳተፍ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ነው። የኒዮርክ ታይምስ ዘገባ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ወንጀል መሆኑን ለዓለም አሰምተዋል። ይህን ተከትሎ የተወሰኑትን  ከገጹ ላይ የሰረዛቸው ቢሆንም ከአሸባሪው ቡድን ጋር አብሮ እንደሚሰራ በግልጽ አስመስክሯል። ይህን ተግባር የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ምእራባውያንም ይሁን ተንታኞቻቸው ሲያወግዙት አልታየም።

የህወሓትን ቡድን ማንነት በውል የሚገነዘቡና ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሰራጨት ጥረት የሚያደርጉ የውጭ ሀገር ተንታኞች በትግራይ ክልል ስለተፈጸመው ሁኔታ ለማብራራት ወደ ኋላ በመሄድ ጭምር ዳሰሳ በማድረግ ጥልቀት ያለው ትንታኔ እየሰጡ ይገኛል። በአንፃሩ በተለያየ መንገድ ከህወሓት ቡድን ጋር የተሳሰሩ ተንታኞች ህሊናቸውን ሸጠው የአንድ ወገን ስሞታን ብቻ እያስተጋቡ ነው። እውነታው በሂደት ግልጽ እየሆነ መምጣቱ አይቀርምና ምን ጊዜም ከእውነት ጋር መቆም ከታሪክ ተወቃሽነት ይታደጋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም