ህጻናትን ለጦርነት መመልመልና ማስታጠቅ አጥብቆ እንደሚቃወም የሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ

2460

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 9/2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በመመልመልና በማስታጠቅ ማሰማራቱን አጥብቆ እንደሚቃወም የደቡብ ክልል ሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው ዛሬ  ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህጻናትን ለጦርነት መመልመልና ማሳተፍ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጡ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ድንጋጌዎችን መጣስ ነው።

በሀገሪቱ ህጻናት ከጉልበት ብዝበዛ፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲጠበቁ መንግሥት ጽኑ አቋም በመያዝ እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል።

በተለይ ህጻናት የመማር፣ ከጥቃት የመጠበቅና የማደግ መብታቸው እንዲከበር በሀገሪቱ የጸደቁ ህጎች   ተፈጻሚ እንዲሆኑ  ቢሮው እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የህጻናት መብትን ለማስጠበቅ የወጡ ህጎችን የተቀበለች ሀገር መሆኑዋንም አስታውሰዋል።

ሆኖም ይህንን በሚጻረር መልኩ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትን ለጦርነት መልምሎ ማስታጠቁ የአለም ዓቀፍ ህጎችና ድንጋጌዎችን ጥሰት በመሆኑ  ቢሮው አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና መንግስታትም ጉዳዩን በቸልታ ከመመልከት ይልቅ ድርጊቱን ሊያወገዙት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ህጻናትን ያለዕድሜያቸው ለጦር የመለመለው፣ ያስታጠቀውና ያሰማራው ይሄው አሸባሪ ቡድን በህግ እንዲጠየቅም አመልክተዋል።

የህፃናቱ ወላጆችና አሳዳጊዎች የህወሓትን አፍራሽ ሴራና ተንኮል በውል በመረዳት ልጆቻቸውን  ካለማቅማማት ሊታደጉ እንደሚገባ   ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።