የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች አስታወቁ

70

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 9/2013 (ኢዜአ) የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በሐረሪ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች አስታወቁ።

ጁንታው ሕጻናትን ጦርነት በመማገድ በሚፈጽመው ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ነዋሪዎች እንዳስታወቁት፤ የሀገር አንድነትን ለመጠበቅ መንግሥት ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።

ከነዋሪዎቹ መካከል ሻምበል ማሞ መታፈሪያ በሰጡት አስተያየት፤ መንግሥት የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን ለማስቻል የጥሞና ጊዜ መስጠቱ ተገቢ እንደነበር አውስተዋል።

ሆኖም ይህንን እንደ ሽንፈት በመቁጠር ወረራ ለመፈጸምና ለመስፋፋት እንደተጠቀመበት ተናግረዋል።

መንግሥት የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ድርጊት ለማስቆም እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥትና ሕዝብ ተቀናጅተው አሸባሪውን ቡድን ለመግታት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ማስረሻ ገብረአምላክ በበኩላቸው፤ የጁንታው እኩይ ድርጊት በአማራ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተቃጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱም ከአባቶቹ የወረሰውን አልበገሬነት በተግባር ላይ በማዋል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መሰለፍ እንዳለበት አመልክተዋል።

ወጣት አብዱረህማን መሐመድ፤ በሰሞኑ ጁንታው የኢትዮጵያ አንድነትን ለማፈራረስ እያደረገ ያለው ጥረት በሕዝቡ እንደሚመክት ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጿል።

በዚህም መንግሥት የሚያቀርበውን ጥሪ ለመቀበል መዘጋጀቱን ያስታወቀው ወጣቱ፤ መንግሥትም የጁንታውን እንቅስቃሴ ለመግታት እርምጃ መውሰድ አለበት ብሏል።

ሌላው የሐረሪ ክልል ነዋሪ ተማሪ አቤል ዮሐንስ ሕጻናት ወደ ትምህርት መግባት ሲገባቸው ለጦርነት መማገዳቸው እንዳሳዘነው ገልጾ፣አሸባሪው ቡድን በሕጻናት ላይ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል ዓለም አቀፍ ተቋማት ማውገዝና ህጻናቱን መታደግ እንዳለባቸው ተናግሯል።

ጁንታው ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ የሚያደርገው ጦርነት በዓለም አቀፍ ሕጎች ጭምር መጠየቅ አለበት ያሉት ደግሞ አቶ ማስረሻ ገብረ አምላክ ናቸው።

መንግስትም የአሸባሪውን ቡድን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማሳወቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም