21ኛው የቶታል ኢነርጂ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል

88

ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) 21ኛው የቶታል ኢነርጂ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የውድድሩ ምዘገባ የፊታችን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን፤ የመመዝገቢያ ዋጋውም 590 ብር መሆኑ ተገልጿል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳግም ተሾመ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ውድድሩ 10 ኪሎ ሜትሮችን እንደሚሸፍንና 25 ሺህ ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል 500ዎቹ አትሌቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ በውድድሩ የኤርትራ፣ ኬንያና ኡጋንዳ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።  

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር እንዲቀንስ በመደረጉ ምክንያት የመመዝገቢያ ክፍያ ዋጋው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ውድድሩ ሲቃረብ የሚኖረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የስርጭት ሁኔታ ታይቶ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በውድድሩ ላይ "ጽዱ" በሚል መሪ ሃሳብ ሰዎች በየመንገዱ እንዳይጸዳዱ መልእክት ያስተላልፋልም ተብሏል።

በሌላ ዜና  ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር "የ3 ኪሎ ሜትር የእለት ተለት እርምጃ ፕሮግራም" የሚል ሀገር አቀፍ ዘመቻ ይፋ አድርገዋል።

ዘመቻውን ያስጀመሩት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራት አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴና የትራንስፖርት ሚኒስቴሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።

የዘመቻው ዓላማ ዜጎች በቀን ቢያንስ ሶስት ኪሎ ሜትር በእግራቸው እንዲጓዙ የሚያበረታታ ነው ተብሏል።

ይህም ማህበረሰቡ ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖረው ከማገዙ ባሻገር በከተሞች ያለውን የትራፊክ መጨናነቅና ከትራንስፖርት እጥረት እንደሚያቃልል ተጠቁሟል።

ዘመቻው በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ የሚጀመር ሲሆን፤ በሂደትም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚሰፋ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም