የባቡር መስመር ዝርጋታ ድርጅት ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅሞቻቸውና ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዳልተከበሩላቸው ገለጹ

71
ደሴ ነሃሴ 1/2010 በያፒ መርከዚ አዋሽ አርባ፣ ኮምልቻ ወልዲያ፣ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ድርጅት ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅሞቻቸውና ሰብአዊ መብቶቻቸው ባለመከበራቸው ለችግር መዳረጋቸውን ገለጹ፡፡ ቁጥራቸው 500 የሚሆን ሠራተኞቹ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ የሥራ ማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ በሾፌርነት የሚያገለግሉት አቶ ታዲዮስ ጋሻው እንዳሉት ድርጅቱ ለተመሳሳይ የሥራ መደብ የተለያዩ ክፍያዎችን በመፈጸም በሠራተኞች መሀል መተማመን እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ የሥራ መስክ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ከ2 ሺህ ብር ያልበለጠ ክፍያ ሲያገኙ በአንጻሩ የውጭ ዜጋ ለሆኑ ቱርኮችና ፊሊፒኖች ከ40 ሺህ በር በላይ እንደሚከፍል ገልጸዋል፡፡ በየዓመቱ የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪም ለታይታ ካልሆነ በቀር ከ25 ሳንቲም ያልበለጠ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ታዲዮስ አስፈላጊ የሆኑ የደህንነት አልባሳት በወቅቱ እንደማይደርሷቸውም ተናግረዋል፡፡ በድርጅቱ የክሬን ኦፕሬተር የሆኑት አቶ አህመድ ሰይድ በሥራ ወቅት ከባቡር ላይ ወድቀው አደጋ ቢደርስባቸውም የሕክምና ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መገደዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ " መብቴን በህግ ለማስከበር ጥረት ሳደርግም ከስራዬ እንደምባረር ማስፈራሪያ ደርሶኛል " ይላሉ ፡፡ በተለይ የጉልበትና የሹፍርና ሥራዎች ላይ የውጭ ዜጎች በስፋት መሳተፋቸው ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንዳያገኙ እያደረገው ስለሆነ መንግስት በዚህ ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጽዳት ሠራተኞች የሚከፈለው አንድ ሺህ ብር ብቻ በመሆኑ ከወቅቱ የኑሮ ውድነት ጋር ህይወታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ወይዘሪት ሰአዳ አህመድ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ተናግረዋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለመቻሉ ለመብቶቻቸው አለመከበር እንደምክንያት የገለጹት ሠራተኞቹ የሠራተኛ ማሕበሩ ለቀጣሪው ድርጅት እንጂ በደል ለሚደርስበት ሠራተኛ እንደማይቆረቆር ተናግረዋል ፡፡ የድርጅቱ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው ማኅበሩ ከድርጅቱ ጋር በሠራተኛው ጥቅምና የዲስፕሊን ጉዳይ ላይ የሕብረት ስምምነት ብናደርግም ድርጅቱ የሰራተኛውን መብት ወደጎን ትቶ የዲስፕሊን ርምጃ ላይ ብቻ ማተኮሩ በሠራተኛው ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ "ማሕበሩ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ያለውን ከፍተኛ የደመወዝ ልዩነት እንዲሁም የሠራተኛው ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር  የአቅሙን ሁሉ አድርጓል" የሚሉት አቶ መሐመድ ችግሩ ድርጅቱ ቃል የገባቸውን ስምምነቶች መፍታት አለመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በእዚህም በተደጋጋሚ ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤት አልባ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ሠራተኞቹ ከሰዓት በኋላ ከኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርና ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በእዚህም የያፒ መርከዚ ባልደረባ ከሆኑ የቱርክ ተወላጆች ሰብአዊ ጥሰትና ብሔራዊ ክብርን የሚያንቋሽሹ ተግባራት እንደሚፈጸሙባቸው ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጌትነት ሽፈራው ሠራተኛው ያለምንም ረብሻ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡን አድንቀው ከሰብአዊ ጥሰት ጋር ተያይዘው የተነሱት ቅሬታዎች ተጣርተው በአፋጣኝ በህግ አግባብ እንዲፈቱ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ከበደ ይመር በበኩላቸው " ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የሠራተኛው ጥቅሞችና መብቶች እንዲከበሩ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው ተፈጸሙ የተባሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችና አሰራሮች በመረጃና በምርመራ ተደግፈው አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው መምሪያው የሚመለከታቸውን በማነጋገር ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡ በእለቱ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የያፒ መርከዚን ከፍተኛ አመራር አካለት በውይይት መድረኩ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፤ የአዜአ ሪፖርተር በአካል ሄዶ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ትናንት 10 የሠራተኛ ተወካዮችን የመረጡ ሲሆን ዛሬ ውይይት በማድረግ በነገው ዕለት የመጨረሻ ምላሹን ለማሳወቅ ተስማምተዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ከደቡበ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና ሰሜን ሸዋ የተውጣጡ 500 የሚደርሱ ሠራተኞች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም