ተማሪዎች በቤተ-ሙከራ ውስጥ የሚጠቀሙበትን ማሽኖች በአገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሪን ማስቀረት ተችሏል-የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

122

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8/ 2013 (ኢዜአ)የኢንጅነሪንግ ተማሪዎች በቤተ-ሙከራ ውስጥ የሚጠቀሙበትን ማሽን በአገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሪን ማስቀረት መቻሉን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገለጹ፡፡

ተቋማቱ ይህን የገለጹት በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር "ወደ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በጉባኤው ላይ በአገሪቷ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የሰሯቸውን የተለያዩ የፈጠራ ስራ አቅርበው አስጎብኝተዋል፡፡

በዚሁ ጉብኝት ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተለያዩ ተቋማት ያመጧቸውን የፈጠራ ስራ በመመልከት አስጎብኚዎችንም አነጋግሯል፡፡

ያነጋገርናቸው አስጎብኚዎች እንዳሉትም ከቴክኖሎጂ አኳያ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወጪ ሆኖባቸው ከውጪ ሲገቡ የነበሩ ማሽኖች በአገር ውስጥ በመስራት ተጠቃሚዎች ዘንድ በማድረስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በራሱ አቅም ያመረተው የኢንጅነሪንግ ተማሪዎች በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚማሩበትን ማሽን አስጎብኝቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ማሽኖች ከዚህ ቀደም ከእንግሊዝና ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ሲገዙ እንደቆዩ የገለጸው፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ግን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በራሱ አቅም ማምረት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ማሽኑም በተለይ በመስኖ ፣ በተለያዩ ግድቦችና የመጠጥ ውሃ አወጣጥ ላይ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያገኙም የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ይህን ማሽን በራሱ አቅም በማምረት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወጪን ማስቀረት መቻሉንም ጠቁሟል፡፡

ይህ በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚያገለግል ማሽንም ከውጪ ይመጣበት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲም እስከ አሁን ለ18 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና ለተለያዩ ፖሊ ቴክኒኮች ጋር ተደራሽ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ጂማ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ጊዜያቸው ሳይደርስ ለሚወለዱ ህጻናት ለማሞቂያነት የሚያገለግል ማሽን ማምረቱንም ገልጿል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ማሽኖች ከውጪ አገራት ሲገቡ ከፍተኛ ውጪ ምንዛሪ ወጪ የሚደረግባቸው ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ያን ለማስቀረት ማሽኑን በአገር ውስጥ አምርቶ ለማሰራጨት መዘጋጀቱን አስረድቷል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም ለእይታ ካቀረባቸው የስራዎቹ ውጤት ከሆኑ ማሽኖች መካከል የብረት መበየጃ ማሽን አንዱ ነው፡፡

ማሽኑም በአካባቢ ላይ ከሚገኙ የወዳደቁ ብረቶች የተሰራ መሆኑን የገለጸው ዩኒቨርሲቲው፤ ወጪ ቆጣቢ እና ቀላል በመሆኑም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ ሚችል መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

የየኒቨርሲቲዎቹ ተወካዮች እንዳሉትም በአገር ውስጥ የፈጠራ ክህሎትን በማዳበር አገሪቷ ለማሽን ግዢ ታወጣ የነበረውን የውጪ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረት እየሰሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም