ሕጻናትን ወደ ጦርነት የመማገድ የሕወሃትን የወንጀል ድርጊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ተጠየቀ

2654

ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የሕወሃት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ሕጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ በማስከር ወደ ውጊያ የመማገድ ወንጀል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመለከተ።

ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመጣስ ህጻናትን ወደጦርነት ያሰለፈውን የሕወሃት ሃይል በዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።

ቡድኑ ለ27 ዓመታት መንበረ ስልጣን በተቆጣጠረበት ዘመን ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ የወንጀል ድርጊቶችን ወደሽብር ቡድንነት ከገባ በኋላም አባብሶ ቀጥሏል።

ከሰሞኑም የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በተጻረረ መልኩ መልከ ብዙ ወንጀሎችን እየፈጸመ ስለመሆኑ በገሃድ ተስተውሏል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ የሕወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ባለፈ አሁን ደግሞ ህጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ አስክሮ ለጦርነት እያሰለፈ የወንጀል ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

“እድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሱ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን ወደጦርነት ማስገባት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተጻረረ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት ነው” ብለዋል።

ህጻናት የነገ አገር ተረካቢዎች እንጂ ካለ አድሜያቸው በጦርነት እንዲሞቱ ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገ ወንጀል ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ዓለም ቀፍ ወንጀል በዝምታ መመልከቱን አንስተዋል።

እ.አ.አ 2002 ላይ በሥራ ላይ የዋለው እና ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን፤ አገራት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

ከዚህ ቀደም ብሎ መንግስት በሽበር ቡድኑ ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባልተጨበጠ መረጃ በትግራይ ክልል የህጻናት ተቆርቋሪ በመምሰል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረጋቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል።

መንግስት ለበርካታ ዓመታት የሚሆን በጀት በማውጣት በትግራይ ክልል እያደረገ የነበረውን ሰብዓዊ ድጋፍም ሲያጣጥሉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

በተቃራኒው አሁን ደግሞ ህጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ በማስከር ለውጊያ ሲያሰልፍ ዓለም አቀፍ ወንጀል መሆኑን እያወቁ ዝምታን መምረጣቸው ይባስ ብሎም እንደጀብዱ በሚዲያዎቻቸው ማስተጋባታቸው አሳዛኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ ህጻናትን ወደውጊያ የማስገባት ወንጀልን በዝምታ ማለፍ በአገር ሞራል ላይ መረማመድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን ሰብዓዊ ወንጀል ያለማውገዝና የድርጊቱ ተባባሪ የመሆን ዝንባሌ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትለማና ህዝብ ከህዝብ እየተጋጨ እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚጠቁምም ተናግረዋል። “የሽብር ቡድኑ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ታዳጊዎቸን ወደውጊያ በማስገባት ዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅ ልንሰራ ይገባል” ብለዋል።