የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2013 በጀት ዓመት ከ600 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ

58

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2013 በጀት ዓመት ከ600ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት በ39 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን አስታወቀ።

በተያዘው በጀት ዓመት ዘመናዊ የግብይት ስርዓትን በመከተል የማዕድን ግብይት እንደሚጀመርም የምርት ገበያው ገልጿል።

ምርት ገበያው ይህን ያስታወቀው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንዳሉት፤ ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ 614 ሺህ 586 ሜትሪክ ቶን ምርት በ39 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።

አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንፃር ሲታይ በመጠን 96 በመቶ በዋጋ ደግሞ 102 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ ለግብይት ከቀረቡ ምርቶች መካከል 35 ነጥብ 5 በመቶ ቡና መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰሊጥ 31 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

ምርት ገበያው ለግብይት የቀረቡ ምርቶችን በመመርመር 68 ሺህ 391 የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

ምርት ገበያው ከሚሰጠው የአገልግሎት ክፍያና ከሌሎች ተግባራት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ግብር በመሰብሰብ ለመንግሥት ገቢ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት እንዲያገኙ ለማስቻል በተከፈተው ልዩ የግብይት መስኮት አማካኝነት 430 ሺህ 680 ኩንታል አኩሪ አተር በ990 ሚሊዮን ብር ማገበያየቱንም ተናግረዋል።

ምርት ገበያው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአጠቃላይ 775 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንና ይህም ከእቅዱ 106 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል።

ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው ያብራሩት።

በበጀት ዓመቱ የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ግብይት ስርዓቱ መካተታቸውን ገልፀው፤ ወደ ግብይት ስርዓቱ ሊገቡ የሚችሉ ተጨማሪ አስር ምርቶች ላይ የአዋጭነት ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

ምርት ገበያው የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 25 እንዲሁም ክልላዊ የኤሌክትሮኒክስ ማዕከላቱን ብዛትም ወደ ስድስት ማሳደጉን ገልፀዋል።

የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት ምርት ገበያው ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር ቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋሙንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ምርት ገበያው በተያዘው በጀት ዓመት ኦፓል፣ ሳፋየርና ኤመራልድ ማዕድናትን ማገበያየት እንደሚጀመርም ነው የገለጹት።

የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም