የበጀት ድልድሉ የብር የመግዛት አቅም በመቀነሱ ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ አድርጓል - የምጣኔ ሃብት ምሁራን

146

ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) የፌደራል መንግስት የ2014 በጀት ድልድል የብር የመግዛት አቅም በመቀነሱ ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ሙስናና ብልሹ አሰራር በኑሮ ውድነት ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ማቃለል እንደሚገባም ተናግረዋል።

561 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሆኖ የጸደቀው በጀቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ጭማሪ አለው።

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ይልቃል ዋሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጀቱ በኢትዮጵያ በ20 በመቶ የቀነሰውን የብር የመግዛት አቅም ታሳቢ አድርጓል።

ኢኮኖሚውን ለሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች የሚመደበው የተጋነነ በጀት የዋጋ ግሽበቱን እንዳያባብሰው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም የአምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ እንዲሆን በመደገፍና በንግድ ስርዓቱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ግሽበቱን ማቃለል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበቱን ከ10 በመቶ በታች ማውረድ ከተቻለ ለኢኮኖሚ እድገቱ ስጋት እንደማይሆንም ጠቁመዋል።

"መንግስት የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ፍትሃዊ የንግድ ውድድር መዘርጋት አለበት" ብለዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ መዚድ ናስር ሙስናና ብልሹ አሰራር በአገልገሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎት ለማግኘት ሙስና የሚከፍሉ አንዳንድ ድርጅቶች ሙስና የሚከፍሉትን ገንዘብ እንደ መደበኛ ወጭ በመውሰድ በምርታቸው ላይ ዋጋ እንደሚጨምሩም በመግለጽ፤ ሙስና በዜጎች የእለት ተለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረ ገልጸዋል።

"የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማዘመን የዜጎች ፈተና የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ማቃለል ይገባል" ብለዋል።

ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ብቻ በመጠቀም የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እንደማይቻል ጠቅሰው፤ "አገልግሎት ሰጭና ተቀባዩ በ'ኦን ላይን' እንዲገናኙ በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት ይገባል" ብለዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ምጣኔ ሀብትና ስራ አመራር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ካሳ ተሻገር የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር ያደረገውን የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደስራ እንዲገቡ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በሀገር ውስጥ ላሉ ግዙፍ አምራች ፋብሪካዎች የሚውሉ ጥሬ እቃዎችን በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ለማምረት ፋብሪካዎች ከአርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የዘይት ፋብሪካዎችን አቋቁሞ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ ለማስገባት መሞከር በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደሚፈጥር ለአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም