"ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ" ለቃል ኪዳኑ ፀንቶ ሕይወቱን ያጣው ጀግና

106

መልከ ብዙ ውስጣዊ ሳንካዎች፤ ዘርፈ ብዙ ዓለማቀፋዊ ጫናዎች በበረቱበት 2013 የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጉዳይ 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' እንዲሉ ለብዙዎች ስጋትና ፍርሃት ጭሮ ነበር።

በዘንድሮ ምርጫ 'ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ነው' በሚል ወደ ስራ ሲገባ የምርጫዊ ሰላማዊነት ክዋኔና አገራዊ ድህንነት ጉዳይ ለጸጥታ አካላት ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ለምርጫው ሰላማዊነት ዕለታዊ የፖሊስ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ጠንካራ አመራር አባላት መካከል ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ሞላ አንዱ ነበር።

ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ በህዝብና መንግስት የተጣለበትን አገራዊ ሃላፊነት የሚወጣበትን ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ዋዜማ ላይ የጤና እክል አጋጠመው።

በፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ምርመራ ሲደረግለትም ሳንባው ውሃ በመቋጠሩ በሆስፒታሉ ተኝቶ ህክምናውን መከታተል እንዳለበት በሀኪሞች ተነገረው።

የ34 ዓመቱ ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ግን ህመም ላይ ቢሆንም ብዙ ተስፋና ስጋት ያዘለው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በመሻቱ 'ህክምናዬ ከምርጫ በኋል ይደርሳል፤ የህዝብ ሰላም ይቀድማል' በሚል ወደ ሥራው ተመለሰ፤ የህዝብ ጸጥታና የአገር ሰላምን አስቀደመ።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ጣቢያዎች ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣ ባልደረቦቹ እማኞች ናቸው። የፖሊስ መኮንኑ፤ በጃንሜዳ አካባቢ ወንጀል መከላከል ኃላፊም ሆኖ አገልግሏል።

አንድ ሃላፊነት ላይ ያለ ባለሙያ 'ለውጥ ያመጣል' በሚል ከባድ ህመሙን ተቋቁሞ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በስኬታማነት እንዲጠናቀቅ እስከ ምርጫው ዕለት በስራ ገበታው ላይ ነበር።

ለአገሩ ሰላም ሲሻ የግል ጤናውን ለይደር ያቆየው የፖሊስ መኮንን በምርጫው ዕለት የተሰጠውን ሃላፊነት እየተወጣ እያለ በድንገት ወደቀ።

የግዳጅ ጓዶቹም ተረባርበው ወደ ሆስፒታል ወሰዱት። ሆኖም የረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ህይወትን መታደግ አልተቻለም።

ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ አገሩ እንድታሸንፍ የማትተካዋን ውድ ሕይወት ሰጠ፤ በቃል ኪዳኑ ጸና።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ገዛህኝ ጌታነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ከራሱ የግል ጤንነት ይልቅ በአገር የተሰጠውን ኃላፊነት አስቀድሟል።

"እኔ ሆስፒታል አልተኛም በሚል ህይወቱን አጥቷል፤ የእርሱ አርዓያነት ለሁሉ የሚተርፍ ነው" ይላሉ።

ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ከባለቤቱ ወይዘሮ አባው ሃይሌ አንዲት ሴት ልጅ አፍርቷል።

በሙያው ምስጉንና ታታሪ እንደነበር የሚያነሱት ወይዘሮ አባው፤ ሀኪሞች አልጋ ይዞ ህክምና እንዲከታተል ቢመክሩትም ስራውን አስቀድሞ የህክምና ቀጠሮውን ለድህረ ምርጫ ማራዘሙን ያስታውሳሉ።

የረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ አሟሟት ለባልደረቦቹ አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ ሆኗል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሃና የሺንጉስ ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ከጤንነትቱ በላይ የአገርን ሰላም በማስቀደም ራሱን መስዕዋት ማድረጉን ነው የተናገሩት።

እንደዶክተር ሃና ገለጻ፤ ክፍለ ከተማው ለቤተሰቦቹ የ100 ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል። በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

"ብዙዎች ሊከፋፍሉና ሊበታትኑ" የሚፈልጓትን አገር ሰላሟን ለማስጠበቅ "መስዋዕትነት የመክፈልን አርዓያነት ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል" ብለዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር ፈቃዱ የስራ ባልደረቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የመታሰቢያ መርሀ ግብር ተደርጎል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም