ቀጥታ፡

የምእራባውያን የተቀናጀ ተጽእኖ ለምን?

በመንግስቱ ዘውዴ /ኢዜአ/

በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሃት ቡድን በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ካምፖች ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት ከፈጸመ በኋላ መንግስት የሀገር ሉአላዊነትን ለመጠበቅ የህግ ማስከበር ዘመቻ አካሂዷል። ቡድኑ ከ20 ዓመታት በላይ ትግራይን ከጥቃት ሲጠብቅ በቆየው መከላከያ ሠራዊት ላይ እንደ ወራሪ በመቁጠር ድንገተኛ አደጋ አድርሶበታል። ዓላማውም ወደ ቀድሞው ስልጣን ተመልሶ ለመምጣት አሊያም ሀገር ለማተራመስ በያዘው አጀንዳ ነው። ይህንን በተለያዩ ጊዜያት ሲናገር የቆየ ቢሆንም በቅርቡ አቶ ጌታቸው ረዳ “ዋና ዓላማችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነው፤ የመጨረሻ አላማችን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ደርሰን መመለስ ካለብንም እናደርገዋለን” በማለት በሙሉ እርግጠኝነት ስለመናገራቸው መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።

ምእራባውያን ሀገራት በተለይ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የሕወሓትን ታሪክ ከመነሻው ጀምሮ የሚያውቁት ቢሆንም ባህሪውን ከማጋለጥ ተቆጥበዋል። ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በየዓመቱ ሲያወጧቸው የነበሩ ዓመታዊ ሪፖርቶቻቸውን ማየት ይቻላል።

ቡድኑ የትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ከሰብአዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ ሲፈጽማቸው የነበሩ ጥሰቶች ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ለዓለም ይፋ አድርገዋል። ቢቢሲ ‘Ethiopia famine aid 'spent on weapons' በሚል ርእስ ባስነበበው ሰፋ ያለ ዘገባ የህወሓት ቡድን በትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት በሱዳን በኩል ሲገባ የነበረውና ለትግራይ ህዝብ እርዳታ በሚል ከተላከው 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 95 ሚሊዮን ዶላር ለጦር መሳሪያ ግዥ እንዲውል ማድረጉን ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህንኑ ጉዳይ CIA የተሰኘው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ማረጋገጡን በዘገባው አስፍሯል። በወቅቱ ድጋፉን በማሰባሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ቦብ ጊልዶፍም ድርጊቱ መፈጸሙ እጅግ እንዳሳዘነው መግለጹ ይታወቃል።

መንግስት በትግራይ ክልል ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱ ተደራሽ ለማድረግ በሚል ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ቡድኑ ግን ውጊያ እንደሚቀጥል ግልጽ አድርጓል። ቡድኑ በሽምቅ ውጊያ በነበረበት ወቅት ሕዝቡ በረሐብ እያለቀ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ እያሰራጨ የነበረ ሲሆን የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ የረሐቡን አጀንዳ ወደ ጎን ጥሎ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀምሯል። ለዚህም ሕጻናትንና ወጣቶችን እያሰለፈና በአደንዛዥ ዕጽ ጭምር እየተጠቀመ ወደ ጦርነት ማስገባቱን ቀጥሏል።  በዓለም አቀፉ ህግ መሰረት ሕፃናትን ለጦርነት መጠቀም የተከለከለ ሲሆን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደ ወንጀል ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን ምእራባውያኑ ይህንን ጉዳይ በዜና መልክ በማሰራጨት ለቡድኑ ማነቃቂያነት ከመጠቀም ባሻገር ወንጀል መሆኑን እንኳ አልጠቀሱም። 

ምእራባውያኑ እነዚህን የመሳሰሉ ውስብስብ ችግሮችን በተለይም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ስለፈጸመው የጭካኔ ተግባር፣ በማይካድራና በሌሎች አካባቢዎች ስለተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ግልጽ የጦርነት አዋጅ ሲናገር አይተው እንዳላዩ በማለፍ ድብቅ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሲሰሩ ይታያል። ይልቁንም ቡድኑ የሚያሰራጫቸው ፕሮፓጋንዳዎችን በማስተጋባት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው አበክረው እየሰሩ ይገኛሉ። ምእራባውያን ሀገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ላለፉት ስምንት ወራት እጅግ በተናበበ መንገድ “የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የዘር ማጽዳት፣ የጦር ወንጀል፣ የእርዳታ ክልከላ ወዘተ” የሚሉ ቃላቶችን በመደርደር “ጉዳዩ እንደሚያሳስባቸው” በመግለጽ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ሀገራቱ መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው የህወሓት ቡድን ጋር “ድርድር መካሄድ አለበት” በሚል ተደጋጋሚ ግፊት ማድረጋቸውን  አጠናክረው ቀጥለዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዘለግ ያሉ ትንታኔዎችን በመጻፍ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም “THE WESTERN CONSPIRACY TO WEAPONIZE FAMINE FOR REGIME CHANGE IN ETHIOPIA” በሚል ርእስ በቅርቡ በፃፉት ጽሑፍ ላይ ምእራባውያን ሀገራት በተቀናጀ መንገድ በኢትዮጵያ ላይ አዲስ ዘመቻ መክፈታቸውን አስፍረዋል። እነዚህ ሀገራት መንግስት በትግራይ ክልል ያደረገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በሰብአዊ መብት ሽፋን ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ሲሰሩ መቆየታቸውን በጽሑፋቸው ላይ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መልኩን በመቀየር “ረሃብን ለጦርነት ዓላማ” በሚል መንግስት ላይ አዲስ ዘመቻ መክፈታቸውን ያስረዳሉ።   ዋነኛ ግባቸውም የመንግስት ለውጥ ማድረግ አሊያም ህወሓትን ወደ ስልጣን መመለስ እንደሆነ በጽሑፋቸው አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም በትንታኔያቸው ላይ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም በሰብአዊ መብት ጥሰት ሽፋን ጫና የሚፈጥሩባቸው ቃላቶችን በመፈብረክ በየመገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኩል በማሰራጨት ኢትዮጵያን በረሃብ ስም እንደፈለጉ ለማድረግ ሌት ተቀን እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

በቅርቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ߵየኢትዮጵያ መንግስት አንድም የህገ-መንግስቱን ክፍል መንካት አይችልም፤ አሁን ካለው የክልሎች ወሰን ላይ መቀነስም ይሁን መጨመር አይችልም ብሏል። አክሎም ኢትዮጵያ የውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኗንና የውጭ ድንበሯን መለወጥ እንደማትችል ገልጿል። ከዚህ አልፎም የአማራ ልዩ ሃይል ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የሚል ትእዛዝ አስተላልፏል።

ይህ በሌላ ሀገር ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ሉአላዊነትን መገዳደር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ ሀይሎችን በሀገሪቱ የትኛውም ግዛት አካባቢ የማሰማራት ሙሉ ስልጣን አለው። መንግስት ይህን ሀሳብ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ በመጥቀስ ባለመቀበሉ የጉዞ ማዕቀብ ዕገዳ እስከመጣል የደረሰ እርምጃ መውሰዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዮናስ ዘውዴ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር እየሞከሩ ያለው ተጽዕኖ አንድ ከእጅ ሊያመልጥ ያለን አገር የማሳደድ አንድምታ ያለው የሚመስል ጫና መሆኑን ነበር የገለጹት።

ምእራባውያን በሰብአዊ መብት ሽፋን በሀገራት በቀጥታ ጣልቃ በመግባት የሚፈልጉትን እንደሚያሳኩ የተለያዩ ሀገራትን ማየት ይቻላል። ምእራባውያኑ በሶሪያ ያቀጣጠሉት እሳት ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ሀገሪቱ ፈራርሳ ዜጎቿም ለሞትና ለስደት ተዳርገዋል። በተመሳሳይ በሊቢያ በየመን፣ በሊባኖስ፣ በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በኢራን፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን በመሳሰሉት ሀገራት ላይ በሰብአዊ መብት ስም እጃቸውን በማስገባት ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ እንደከተቷቸው ይታወቃል። አሁን በኢትዮጰያ ላይ የጀመሩት ዘመቻም ከዚህ የተለየ ፍላጎትና ዓላማ ያለው አይደለም። ምዕራባውያን እውነት ስለ ሰብዓዊ መብት የሚጨነቁ ቢሆን ኖሮ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይም ሆነ በሌሎች ንጹሃን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽም ተጠያቂ ማድረግ አሊያም ማውገዝ ነበረባቸው፡፡

እንግሊዛዊው ጸሃፊ ግራሃም ፔብልስ “Stop Interfering”: Ethiopia’s Opportunity after the Election” በሚል ርእስ በቅርቡ ከምርጫ ጋር በማያያዝ በፃፉት ትንታኔ ላይ ምዕራባውያን ለ27 ዓመታት ሕወሓትን በገንዘብ ሲደግፉ እንደነበር በማስታወስ አሁንም መልሰው ስልጣን ላይ ለማምጣት እያሴሩ መሆኑን ይዘረዝራል። ጸሀፊው አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፖለቲካ ተንታኞቻቸው፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም የአረቡም ሆነ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን አሸባሪውን ቡድን በመደገፍ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ግልጽ ጣልቃ ገብነት እያሳዩ መሆኑን አመልክተዋል። አክለውም አሁን ላይ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽን ላለማስከፋት እንዲሁም ቻይና በአፍሪካ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ተጽዕኖ እየፈጠረች በመምጣቷ ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር እንደሚፈልጉ በመጥቀስ ሀገሪቱ በብሔር እንድትከፋፈል እንጂ በልማት አብባ ማየት እንደማይሹ በግልጽ አሳይተዋል።

ምእራባውያን ሀገራት ዋነኛ አጀንዳቸው ኢትዮጵያን ማዳከምና እነርሱ በሚፈልጉት ቅርጽ የሚመሰረት ደካማ መንግስት መፍጠር ነው። ለዚህም ሕዝብን በመከፋፈል እና በሰብአዊ መብት ሽፋን መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር ድርድር እንዲያደርግ ከምንጊዜውም በላይ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ተጽእኖ መቋቋም የሚቻለው ህዝቡ በአንድነት መቆም ሲችል ብቻ ነው። በመሆኑም መላው የሀገሪቱ ህዝብ ከወትሮው በበለጠ ትኩረቱ አንድነቱ ላይ መሆን አለበት።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም