ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ምስራቅ ሪጅኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር እያካሄደ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 06/2013 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ምስራቅ ሪጅኑ " ኢትዮጵያን እናልብሳት" ፕሮግራምን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

ካምፓኒው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብሩን እያካሄደ ያለው በስር  በሚገኙ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት መስጪያ  አካባቢዎች ነው።

በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ምስራቅ ሪጅን የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ማናዬ እንደገለጹት፤  በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሪጅኑ ከ60ሺህ በላይ ችግሮች ለመትከል ታቅዷል።

ዛሬው በሪጅኑ  በተጀመረው መረሃ ግብር ከ10ሺህ በላይ የደንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል ከ2ሺህ በላይ የሪጅኑ ሠራተኞች  መሳተፋቸውን  ተናግረዋል።

አምና በሪጅኑ ደረጃ 29 ሺህ ችግሮች መተከላቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ችግኞቹ እንዲፀድቁ ሠራተኞችን በመቅጠር በተደረገው እንክብካቤ  60 በመቶው ማጽደቅ መቻሉን አስረድተዋል።

ዛሬ በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ብቻ  6ሺህ ችግኝ ለመትከል አቅደው ማከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ በሪጅኑ የፋይናንስ ዘርፍ ሀላፊና የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሸዋረጋ ሽፈራው ናቸው ።

አምና በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የተከልነው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው  ፀድቋል ያሉት አቶ ሸዋረጋ፤ ዘንድሮ የተከሏቸውም ተንከባክበው  እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል።

በሪጅኑ ስር በሚገኙ ከ50 በላይ የአገልግሎት መስጪያ ወረዳዎችና ከተሞች ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም