“ክብር ለሀገር መከላከያ” በሚል መርህ ለአስር ቀናት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጀመረ

1035

ሐምሌ 6/2013 (ኢዜአ) “ክብር ለሀገር መከላከያ” በሚል መርህ በአስር ቀናት ውስጥ 300 ሺህ ችግኞች የመትከል መርሀ ግብር በዛሬው እለት ተጀመሯል።

የመከላከያ ሰራዊት እና የተቋሙ አመራሮች በየካ ሚሊኒየም ፓርክ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አከናውነዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሰራዊቱ ሀገራዊ ግዳጁን እየተወጣ ጎን ለጎን በሀገር ልማት ላይ አሻራውን እያሳረፈ ይገኛል።

የመከላከያ ሰራዊት የሃገር ህልውና እንዲቀጥልና አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ደሙን በማፍሰስና መስዋዕት በመሆን እዚህ ስላደረሰን ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ ከመደበኛ ተልዕኮው ጎን ለጎን በማህበራዊ ስራዎች ላይ በመሰማራት ህዝቡን እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አሁንም በኢትዮጵያን እናልብሳት መርሀ ግብር ይህንኑ ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክቶሬት ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል አስፋው ማመጫ፤ አገርን አረንጓዴ የማልበስ ጉዳይ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸ አካባቢ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

የህዝቡ ድጋፍ ለሰራዊቱ ከፍ ያለ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ገልጸው ለአገሩ ልማት ድጋፉን በማጠናከርና እንዲሁም አገሩን በማስከበር ሂደት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በችግኝ ተከላ ላይ ያገኘናቸው የሰራዊቱ አባላት፤ ይህ ተግባር ከገባነው ቃለኪዳን አንጻር ጥቂቱ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለመጭው ትውልድ የለማች፣ የበለጸገችና አረንጓዴ አገር እናስረክባለን ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከአንድ የግል ድርጅት የ3 ሚሊየን ብር ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡

በችግኝ ተከላው የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት ተገኝተዋል።