በኢትዮጵያ ዴልታ የተባለው ሶስተኛው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል- ዶክተር ሊያ ታደሰ

61

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 06/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዴልታ የተባለው ሶስተኛው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ሊከሰት ስለሚችል ከሚያደርሰው ጉዳት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

ሚኒስትሯ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሁን ያለበትን ሁኔታና እየተሰጠ ያለውን ክትባት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ አልፋና ቤታ የተባሉ ቫይረሶች መኖራቸው በምርመራ ተረጋግጦ ከፍተኛ የመከላከለ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካና በሌሎች አለማት ዴልታ የተሰኘው ሶስተኛ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መከሰቱን ያስታወሱት ዶክተር ሊያ በኢትዮጵያም የመከሰት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ብለዋል።  

በመሆኑም ቫይረሱ ከሚያደርሰው ጉዳት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ዴልታ ቫይረስ በበርካታ አገሮች ካለው ስርጭት አኳያ በኢትዮጵያም ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ ምርመራ መጀመሩና የምርመራ አቅምን ለማጠናከር ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር የቫይረሱን ስርጭት መገደብ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመስጠት በቅርቡ ከ400 ሺህ በላይ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል።  

ህብረተሰቡ  የመጀመሪያውን ክትባት በወሰደበት የጤና ተቋም በመሄድ በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ በክልል ደግሞ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ክትባቱነ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

በቅርቡ ተጨማሪ ክትባቶች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር ሊያ ከዚሀ ቀደም የተገኘው የሲኖፋርም ክትባት ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በመጀመሪያው ዙር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በሁለተኛው ዙር ከ42 ሺህ በላይ ዜጎች የኮቪድ19 ክትባት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡


ክትባቶች በሽታን ከመከለከልና ሊያደርሰው ከሚችለው ጉዳት አንጻር ተመሳሳይ የመከላከል አቅም ያላቸው በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊከተብ ይገባል ብለዋል።

በ20 ደቂቃ የሚደርስ የፈጣን የኮሮናቫይረስ  ምርመራ ማድረጊያ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በመጀመሩ ምልክቱ ያለበትና  ንክኪ ያለው ሰው ሁሉ በነጻ ሄዶ እንዲመረመር ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ 277 ሺህ 137 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ4 ሺህ 343 በላይ ወገኖች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም