ቀጥታ፡

በሃገር ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመመከት ህዝቡ ደጀንነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተገለጸ

ጎንደር፤ ሐምሌ 5/2013(ኢዜአ)በህዝብና በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመደቀን የሚፍጨረጨረውን የትህነግ አሸባሪ ቡድን ለመመከት ህዝቡ በደጀንነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ጠየቁ።

ከንቲባው ዛሬ በጎንደር ከተማ በተከናወነው የሀምሌ 5 ቀን 2008 ዓ/ም ህዝባዊ እንቢተኝነት መታሰቢያ መርሃግብር ላይ እንደተናገሩት የከተማው ህዝብ ያካሔደው ትግል ሃገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ነው።

የጎንደር ህዝብ በህዝባዊ እንቢተኝነት የፈጸመው ተጋድሎ አይደፈሬና አይነኬ የነበረውን የትህነግ አምባገነናዊና የአፈና ስርአት ከህዝብ ጫንቃ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ አሽቀንጠሮ የጣለበት ታሪካዊ ቀን እንደሆነ ገልፀዋል።

አሸባሪው ትህነግ ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ሴራ ለመበጣጠስ ለተሰለፈው ህዝባዊ የመከላከያ ሃይል ህዝቡ በደጀንነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

በተለይም በጎንደርና አካባቢው ትንኮሳ ለመፈጸም የሚፍጨረጨረውን አሸባሪ ቡድን ለመመከት ልጆቹንና ቤቱን ትቶ ለዘመተው የአካባቢ ሚሊሻና ልዩ ሃይል ህዝቡ የስንቅ ድጋፍ በማድረግ የጀመረውን አጋርነት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩም የዘማች ሰራዊት ቤተሰቦችን በመደገፍ በኩል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የእርሻ ስራቸው እንዳይስተጓጎልም ህብረተሰቡን እያሳተፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት እጩ ዶክተር ቹቹ አለባቸው "ሀምሌ 5 የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የማንነት ጥያቄዎች የመንግሰት አጀንዳ እንዲሆን ፈር የቀደደ ህዝባዊ ተጋድሎ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ሀምሌ 5 የወለደው የለውጥ ትግል የመላው አማራና የኢትዮጵያ ህዝብ የመስዋእትነት ውጤት መሆኑን ጠቁመው፤የድሉን ሰማእታት መዘከር ተገቢነት እንዳለውም አስረድተዋል።

“የትህነግ አሸባሪ ቡድን በአማራው ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ ማለቱ ተፈጥሯዊ ባህሪው ጦርነትና የህዝብ እልቂት እንደሆነ በቂ ማሳያ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል”ብለዋል።

መርሃ ግብሩ እለቱን በሚዘክሩ የፓናል ውይይት፣ የችግኝ ተከላና፣ የኪነጥበብ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም