ቀጥታ፡

በሌሴቶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ አደረጉ

ሐምሌ 05/2013 (ኢዜአ) በሌሴቶ  የሚኖሩ  የኢትዮጵያ  ዳያስፖራ ማህበረሰብ  አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ   የ6ሺ 100 ዶላር ቦንድ  በመግዛት ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን ያደረጉት በሌሴቶ ዋና ከተማ ማሴሩ  የሚኖሩ  የኢትዮጵያ  ዳያስፖራ  ማህበረሰብ  አባላት ናቸው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው  ተክለማሪያም በሌሴቶ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር በማሴሩ  ከተማ  በኢትዮጵያ  ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያም ተወያይተዋል።

ለዳያስፖራ ማህበረሰብና ለሌሎች ተገልጋዮች በሚሰጡ አገልግሎቶችና ድጋፎች ዙሪያ  እንዲሁም በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ድጋፎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

አምባሳደሩ በሌሴቶ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዋናነትም ለኮሮና ቫይረስ መከላከል፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት  ማጠናከሪያ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎችእርዳታና መልሶ ማቋቋም ድጋፎችን በማድረግ፣ ለህዳሴ  ግድብ ቦንድ በመግዛት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

የማህበረሰብ አባላቱ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዕውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ማበርከታቸውም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም ኤምባሲ በደቡብ አፍሪካና በተወከለባቸው ሌሎች ስድስት ሃገራት  (ሌሴቶ፣ በኢስዋቲኒ፣ በናሚቢያ፣ በቦትስዋና፣ በሞዛምቢክ እና በማዳጋስካር) ለሚኖሩ  የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብና ለሌሎች ተገልጋዮች በሚሰጣቸው የተለያዩ የቆንስላ አገልግሎቶችና ድጋፎች ዙሪያ ገለጻ ተሰጥቷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በሌሴቶ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት  ከኤምባሲው ጋር በመናበብ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እያካሄዱት ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም