ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ታርሶ ከተዘጋጀው መሬት አብዛኛው በዘር ተሸፈነ

ፍቼ ፤ ሐምሌ 05/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅቱ ታርሶ ከተዘጋጀው 430 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ አብዛኛው በዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፤ምርታቸውን ለማሳደግ የግብርና ሥራቸውን በልማት ባለሙያዎች ታግዘው እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ እንዳሉት፤ በዞኑ  ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች 430 ሺህ 400 ሄክታር መሬት በማረስ ለዘር ዝግጁ አድርገዋል።

በዞኑ በልማቱ ስራ  176 ሺህ አርሶ አደሮች  እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸው ለዘር ዝግጁ የሆነው መሬት ከአምናው በ21 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።

በአካባቢው  ከሰኔ ወር ጀምሮ የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ሂርጳሳ፤ በምርት ዘመኑ ታርሶ ለዘር ከተዘጋጀው መሬት አብዛኛው በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ቀሪው 22 ሺህ መሬት ዘግይተው በሚዘሩ ሰብሎች ለመሸፈን ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ምርታማነቱን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶችን በስፋት ከመጠቀም ባሻገር እንደ ጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ያሉ የእህል ዘሮችን በመስመር እየዘራ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሂርጰሳ ገለጻ፤ በግብአትነት የሚውል ከ5ሺህ ኩንታል የሚበልጥ  ምርጥ ዘርና ከ244 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በሽያጭ ቀርቧል።

በተጨማሪም  1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አርሶ አደሩ የሚጠቀም መሆኑ በምርት እድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

"በዓመቱ በዞኑ በዘር ከተሸፈነው ማሳ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ያሉት" ምክትል ሃላፊው፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ26 በመቶ ብልጫ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች መካከል በደገም ወረዳ የሌመን ቀበሌ ነዋሪ አቶ  ገላን ዱኪ እንዳሉት፤ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን  በአግባቡ ተጠቅመው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የግብርና ባለሙያዎች በቅርብ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረጉላቸው ነው።

የባለሙያዎቹ እገዛ ለምርታማነት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በስልጠና ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተግባር እየሰሩበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋይ ፉላሳ ናቸው።


በወረዳው የስልሚ ቀበሌ ግንባር ቀደም አርሶ አደር ደርቤ ቶልቻም በበኩላቸው፤ የባለሙያን ምክር ሰምተው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ሰብሎችን በማፈራረቅ እንደሚዘሩ ተናግረዋል።  

ሌሎችም አርሶ አደሮች በተመሳሳይ ሁኔታ መሬታቸው ላይ አፈራርቀው በመዝራት ቢጠቀሙ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ካላቸው ተሞክሮ በመነሳት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም