ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ በኢኮኖሚ ማስተሳሰር አለባቸው---በደቡብ ሱዳን የክብር ቆንስላ አቶ አይሸሽም ተካ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ05/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ በኢኮኖሚ ማስተሳሰር እንዳለባቸው በደቡብ ሱዳን የክብር ቆንስላ አቶ አይሸሽም ተካ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ቀጠናውን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት የሁለቱን ሀገሮች ወዳጅነት እንደሚያጠናክረውም ጠቁመዋል።

አቶ አይሸሽም ተካ ላለፉት 17 ዓመታት ኑሯቸውን በጁባ አድርገው የተለያዩ የንግድ ስራዎችን ያከናውናሉ ።

በደቡብ ሱዳን ቆይታቸው በሰላም፣ ልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እኤአ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግስት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲረዳው በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስክ የክብር ቆንስላ ሆነው እንዲሰሩ በሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

ኢዜአ የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን ግንኙነትንናሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ከአቶ አይሸሽም ጋር ቆይታ አድርጓል።

በቆይታቸውም ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሺህ የሚቆጠር በርካታ ኪሎሜትር ድንበር ከመጋራት ባለፈ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተሳሰሩ ሀገሮች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳናዊያን ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ፈጥና የምትደርስ ወዳጅ ሀገር መሆኗንም ነው የተናገሩት።

ደቡብ ሱዳናውያን አጋጥሟቸው የነበረውን የፖለቲካ ቀውስ እንዲሻገሩ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ተጫውታለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አቢይ አህመድ የደቡብ ሱዳን ተፎካካሪ ኃይሎች ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱና በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት በምታደርገው ጥረት ላይ ደቡብ ሱዳን  አጋርነቷን ማሳየቷን አብራርተዋል።

ሁለቱ ሀገሮች ካላቸው የጠበቀ ወዳጅነት አንጻር ደቡብ ሱዳናውያን ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው እንደሚቆጥሯትም ጨምረው ገልጸዋል።

ደቡብ ሱዳናዊያን የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የማይሰጡና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ችግሮችን አብረው የሚጋፈጡ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ በኢኮኖሚ ማስተሳሰር እንዳለባቸውም የክብር ቆንስላው አቶ አይሸሽም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው "የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር" ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ችግኝ ለመላክ መወሰኗ ቀጠናውን በማስተሳሰር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

ደቡብ ሱዳን ይህንን የኢትዮጵያ እቅድ በመልካም ጎኑ መቀበሏን ጠቅሰው፤ መርሃ ግብሩ አማራጭ የዲፕሎማሲ መስክ በመሆን ሁለቱን ሀገሮች በማስተሳሰር ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ደቡብ ሱዳን ነጻ ሀገር ሆኗ ከተመሰረተች ጥቂት ዓመታት በኋላ ያጋጠማት የፖለቲካ ቀውስ የበርካታ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወት መቅጠፉ ይታወሳል።

ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ በኢጋድ ጥላ ስር ከፍተኛ ሚና የተጫወተች ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች ጉዳያቸውን በሰላም እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ደቡብ ሱዳን አሁን ላይ በአንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም