ቀጥታ፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰኔ 15/2011 ዓ.ም ግድያ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የመከላከያ ምስክሮችን መስማት ጀመረ

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 5/2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰኔ 15/2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ በተጠረጠሩት በእነ ሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ የተከሰሱ 32 ተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮች ዛሬ መስማት ጀመረ።

ፍርድ ቤቱ በእነሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ የክስ ሂደታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ 55 ተከሳሾች መካከልም 20ዎቹ ሰኔ 11/2013 ዓ/ም በዋለው ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ መደረጉ ይታወሳል።

በዋና ወንጀል ፈጻሚነት በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ሲታይ የቆየው አንደኛ ተከሳሽ ሻምበል መማር ጌትነት፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይነው ሰፊነው እና 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ይሁኔ ላይ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ መስጠቱ ይታወቃል።

ይህም በወንጀል ድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው በሰውና በአቃቤ ህግ ማስረጃ በመረጋገጡ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

የቀሩት 32 ተከሳሾች ደግሞ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 5/2013 ዓ/ም በሰጠው ቀነ ቀጠሮ መሰረት የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮች ቃል ዛሬ መስማት ጀምሯል።

የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቧቸው አብዛኞቹ የመከላከያ ምስክሮች በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ በመሆናቸው እንዳይመሰክሩ ህጉ ስለሚከለክል የመከላከያ ምስክር ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም የሚል መቃወሚያ አቃቤ ህግ አቅርቧል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፤ አንደኛው ተከሳሽ ለሌላኛው ተከሳሽ እንዳይመሰክር የሚከለክል ህግ የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የቀረቡ የመከላከያ ምስክሮችን እንዲሰማ ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ አንደኛው ተከሳሽ ለሌላኛው ተከሳሽ እንዳይመሰክር የሚከለክል ህግ የሌለ መሆኑን አቃቤ ህግ ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት የመከራከሪያ ጭብጥ መሰረት የቀረቡ የመከላከያ ምስክሮችን ቃል መስማት ጀምሯል።

ዛሬ የቀረቡት ሶስት የመከላከያ ምስክሮችም በሁለተኛ፣ ሰባተኛ፣ 11ኛ፣ 46ኛ እና 48ኛ ተከሳሾች ላይ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ የምስክርነት ቃላቸውን እየሰጡ ነው።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማሰማት የጀመረው የመከላከያ ምስክሮችን የማድመጥ ሂደት በቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም