ቀጥታ፡

አልማ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለማከናወን ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ማሳካት አለመቻሉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 05/2013(ኢዜአ) የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ባለፉት ሁለት ዓመታት ለማከናወን ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ማሳካት አለመቻሉን ገለጸ።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሶስት ዓመታት 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።


አልማ ከሀምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ የህዝባዊ ንቅናቄ ሳምንት እያካሄደ ነው።

የማኅበሩ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ሐሚድ አሕመድ፤ የንቅናቄው ዓላማ የማህበሩን ህዝባዊ መሰረት ለማስፋት፣ የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግና ሀብት ለመሰባሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በማህበሩ የተከናወኑና የተጠናቀቁ ፕሮጀከቶችን ለተጠቃሚዎች ርክክብ ይፈጸማል ብለዋል።

አልማ ከ2012 አስከ 2014 ዓ.ም የሚቆይ ስትራቴጂክ ግቦች አስቀምጦ በ3 ዓመታት ውስጥ 21 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ሀብት በማሰባሰብ የልማት ስራዎችን ገቢራዊ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታትም 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለማሰባስብ አቅዶ  2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብቻ ማሰባሰቡን ነው የተናገሩት።

በሁለት ዓመታት ውስጥ 4 ሺህ 697 የትምህርት፣ የጤና እና የስራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም አቅዶ ማሳካት የቻለው 1 ሺህ 731 ፕሮጀክቶችን ብቻ መሆኑንም አቶ ሐሚድ ጠቁመዋል።

ለእቅዱ አለመሳካት ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣና በጎርፍ አደጋዎች እንዲሁም የግጭት መከሰትን በምክንያትነት አንስተዋል።

ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል 1 ሺህ 691 ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አልማ የክልሉን ህዝብ የማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወነ ባለው ተግባር ላይ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ ማህበሩን ለመደገፍ የጀመረውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው አቶ ሐሚድ ጥሪ ያቀረቡት።

በተጨማሪ የአማራ ባሕል ማዕከል ግንባታ የሚሆን ከ42 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ርክክብ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ነገር ግን ቦታው የግለሰብ፣ የቀበሌና የመንግስት ቤቶች ያሉበት በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ከሶስተኛ ወገን ነጻ እንዲያደርገው ማኅበሩ መጠየቁን ጠቅሰው፤ ይህን ተከትሎም የማዕከሉን ዲዛይን ማውጣትና ሀብት የማሰባሰብ ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም