አዲስ የሚመሰረተው ምክር ቤት የዴሞክራሲ ስርዓትንና የሀገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ይጠበቅበታል-የምክር ቤቱ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚመሰረተው ምክር ቤት የዴሞክራሲ ስርዓትንና የሀገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ይጠበቅበታል-የምክር ቤቱ አባላት
አዲስ አበባ ሃምሌ 05/2013(ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ስርዓትንና የሀገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የ5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዲስ የሚመሰረተው ምክር ቤት አባላት በተግባራቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማስቀደም እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
ወይዘሮ ሳራ አቤ አዲሱ ምክር ቤት የተለያዩ ሃሳቦች የሚነሱበት ግን ዳግም በሀገር አንድነት ላይ የጋራ ትብብር የሚታይበት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመው ሀገር ለማስቀጠል በቆራጥነት ድምጽ የሰጡበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም አንስተዋል።
በመሆኑም በህዝብ ድምጽ አሸናፊ ሆነው ወደ ምክር ቤት የሚገቡ አባላት በአብላጫ ድምጽ በማመን የዴሞክራሲ ስርአት ልምምድ የሚያደርጉበትና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስቀጥሉበት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
አባላቱ የወከሉትን ህዝብ ጥቅም በሚያነሱበት ወቅት የሌላውን መብትና ጥቅም በማይነካና መቻቻልን በሚያንጸባርቅ መልኩ መሆን እንዳለበትም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
አቶ መሃመድ የሱፍ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የሀገር ሃብትና ንብረትን ከምዝበራ ለመታደግ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በማስቀደም የመረጣቸው ህዝብ ከድህነት ለማውጣት መታገል እንዳለባቸውም እንዲሁ።
ወይዘሮ እቴነሽ ዘለቀ፤ አዲስ የሚመሰረተው ምክር ቤት አባላት ህግ በማውጣት፣ በቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የወከላቸውን ህዝብ ድረስ ወርደው በመስራት ረገድ በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት የተጀመረውን ጥረት በማገዝና የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ረገድ አባላቱ በጋራ መቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የ5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዚህ ረገድ ልምዳቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናችውን ጨምረው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት የሚያነሷቸው ሃሳቦች በዜጎች መካከል ልዩነትን እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም አባላቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በየአካባቢያቸው በሚመለሱበት ወቅት በምክር ቤት ቆይታቸው ያገኙት ልምድ ተጠቅመው ህዝብን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ የ484 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል።
በተመሳሳይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብን 5፣ ኢዜማ 4፣ የግል ተወዳዳሪዎች 4 እንዲሁም የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 2 ወንበር ማግኘታቸው ይፋ ሆኗል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ መንግስት መመስረት ይችላል።