የሳተላይት መረጃዎችን ተቋማት ለስራዎቻቸው ስኬት ግብአት እያደረጉ ነው- የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት

95

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃዎችን ተቋማት ለስራዎቻቸው ስኬት በግብአትነት እየተጠቀሙ መሆኑን የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ገለጸ።

ኢኒስቲትዩቱ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ የሕዋ ሳይንስን ከ30 ዘርፎች ጋር የማስተሳሰር እቅድ ተይዟል።

በታህሳስ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ETRSS-01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።

በታህሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ሕዋ አምጥቃለች።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የሺሩን አለማየሁ፤ ኢትዮጵያ ሁለቱን ሳተላይቶች የመሬት ምልከታ ያደረገችው ካሏት ፍላጎቶች አንጻር እንደሆነ ይናገራሉ።

ግብርና፣ መሬት አስተዳደር፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ተፈጥሯዊ አደጋዎችና ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎች ለኢትዮጵያ አስፈላጊ በመሆናቸው ሳተላይቶቹ ይህንን ነባራዊ እውነታ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ሁለቱ ሳተላይቶች መረጃዎችን እየላኩ መሆኑን ጠቅሰው ተቋማትም መረጃዎችን ለስራዎቻቸው ስኬት በግብአትነት እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢኒስቲትዩቱ መረጃዎቹን ለተቋማቱ በነጻ እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ አደጋ ስጋት፣ መሬት አስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር እየተጠቀሙባቸው ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችም የሚያገኟቸውን መረጃዎች ለጥናትና ምርምር ግብአት እያዋሉ መሆኑን ነው ዶክተር የሺሩን ያስረዱት።

የሳተላይቶቹ መኖር ተቋማት ከዚህ በፊት የሳተላይት መረጃዎችን ለማግኘት የሚያወጡትን የውጪ ምንዛሬ ማስቀረቱንና ኢትዮጵያ ከሕዋ የምትፈልጋቸውን መረጃዎች በቀላሉ ለማግኘት እንዳስቻለም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ የሕዋ ሳይንስን ከ30 ዘርፎች ጋር የማስተሳሰር እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ሳተላይቶች በግንቦት ወር 2013 ዓ/ም በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል የተመረቀው የብዝሓ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጋር በማቀናጀት ጣቢያው ከቻይና አምስት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የሚያገኛቸውን መረጃዎችን ኢትዮጵያ እየተጠቀመች እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ያመጠቀችው የመጀመሪያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሕዋ ከሁለት ዓመት ከግማሽ እስከ ሶስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን ሁለተኛው ሳተላይት ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ትቆያለች።

ሁለቱ ሳተላይቶች የተቀመጠላቸውን የቆይታ ጊዜ ካጠናቀቁ በኋላ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆኑ ነው ዶክተር የሺሩን ያስረዱት።

ይሁንና ሳተላይቶቹ አገልግሎት መስጠት ካቆሙ በኋላ ኢትዮጵያ ሶስተኛ ሳተላይቷን እስክታመጥቅ ድረስ ከቻይና አምስት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃዎችን እንደምታገኝ ገልጸዋል።

በተያያዘም ኢትዮጵያ ሶስተኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችሉ የዝግጅት ምዕራፍ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሳተላይቱን ለማምጠቅ የአዋጪነት ጥናትና ሌሎች መሟላት ያለባችውን ቴክኒካዊ ጉዳዮች የመተንተን ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሳተላይት ቁጥሮችን በመጨመር ባጠረ ጊዜ ከሕዋ ጠቃሚ መረጃዎችን የማግኘት ተግባር አጠናክራ ትቀጥላለችም ብለዋል።

በኢኒስቲትዩቱ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ኢትዮጵያ ሶስት ሳተላይቶችን የማምጠቅ ዓላማ አላት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ያመጠቀቻት ETRSS-01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት 64 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሲሆን 13 ነጥብ 7 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል ትችላለች።

በ2013 ዓ.ም ወደ ሕዋ የተላከችው ET-Smart-RSS ሁለተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት 72 ኪሎ ግራም የምትመዝንና 5 ነጥብ 4 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል የምትችል ናት።

በግንቦት 2013 ዓ.ም በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል የተመረቀው የብዝሓ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከአምስቱ የቻይና ሳተላይቶች እስከ 0 ነጥብ 5 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል እንደሚችል በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ጣቢያው ጋኦፈን-1፣ ጋኦፈን-3፣ ጋኦፈን-5፣ ሲ.ቢ.ኢ.አር.ኤስ-4 እና ሱፐርቪው-1 ከተባሉ የቻይና ዓለም አቀፍ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃዎችን ከ15 ደቂቃ እስከ አንድ ሠዓት ባለው ጊዜ እንደሚቀበልም መረጃዎች እንደምትችል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም