የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለመቄዶኒያ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለመቄዶኒያ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሐምሌ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከአንድ ማሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ማዕከሉን በአካል ተገኝተው የጎበኙት የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች የተለያዩ መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁሶችን፣ አልባሳትና ሌሎች የመገልገያ ቁሳቁሶችን ለማዕከሉ አስረክበዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ በቀጣይም የተለያዩ ድጋፎችን ለማእከሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
አረጋውያንና የአዕምሮ ህመምተኞችን ለመርዳት የህክምና ሙያዊ እገዛ ብሎም የግብአት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከማዕከሉ ጋር በመቀናጀት ለህክምና የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለሟሟላትና እገዛ ለማድረግ እንደሚሰሩም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የመቄዶኒያ አረጋዊያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ ኤጀንሲው ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። የመድኃኒት አቅርቦት ችግር፣ የዋጋ መጨመር እና የመድኃኒቶች መጥፋት ችግር እንደሚገጥማቸው አንስተው፤ "የተደረገው ድጋፍ ከፍ ያለ ትርጉም አለው" ብለዋል።