በኢትዮጵያ የኤሮስፔስ ምህድንስና የድህረ ምረቃ ትምህርት መሰጠት ሊጀመር ነው

118

ሐምሌ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኤሮስፔስ ምህድንስና ዘርፍ የድህረ ምረቃ ትምህርት መስጠት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።

የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል ግንባታ ለመጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑም ታውቋል።

የኤሮስፔስ ምህንድስና የአውሮፕላን፣ የጠፈር አውሮፕላን እንዲሁም ከነዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ስርዓቶችና መሳሪያዎች ንድፍ፣ መስራት፣ ማምረትና መፈተሽ ላይ የሚያተኩር የምህንድስና ዘርፍ ነው።  

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የሺሩን አለማየሁ በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ትምሀርት ለመስጠት መታቀዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ትምህርቱ የሚሰጠው ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርስቲው ጋር በ2012 ዓ.ም በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱና ዩኒቨርሲቲው በጋራ በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ ትምህርቱን ለማስተማር የሚያስችል የስርዓት ትምህርት ቀረጻ አዘጋጅተው ለዩኒቨርሲቲው መላኩንና ዩኒቨርሲቲው ውሳኔ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

የኤሮስፔስ ምህንድስና ትምህርት መጀመሩ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ክፍተት ለመሙላት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

በቀጣይም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን ለመስጠት እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል።

በኤሮስፔስ ምህንድስና የሚሰጠው ትምህርት ኢትዮጵያ ለመገንባት ያቀደችውን የሳተላይት ማምረቻ፣ መገጣጠሚያ፣ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ነው ዶክተር የሺሩን ያስረዱት።

ኢንስቲትዩቱ ማዕከሉን ለመገንባት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 30 ሺህ ያህል ካሬ ሜትር ቦታ መውሰዱን አመልክተዋል።

የማዕከሉን ግንባታ ለማከናወን የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ጥናት መካሄዱን ገልጸው፤ የአዋጪነት ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ግንባታውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሀብት ማፈላለግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ሳተላይቶችን ማምረት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሚሆነው የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል በራስ አቅም ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የኤሮስፔስ ምህንድስና የትምህርት ዘርፍ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ እቅድ መያዙን ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ትምህርቱን ለማስጀመር የቀረበው ረቂቅ ሰነድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል እና መካኒካል ኮሌጅ መገምገሙንና የዩንቨርስቲው ሴኔት በሚያደርገው ስብስባ ሰነዱ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ በዓለማችን ራሽያ ብዙ የሰራችና ጥሩ ተሞክሮ ያካበተች እንደሆነች ይነገርላታል፤ በአፍሪካም ደቡብ አፍሪካ በዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም